Tuesday, October 8, 2024
spot_img

መንግሥት በትዊተር ላይ ይፋዊ ቅሬታውን ማቅረቡን አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 22 2014 ― መንግሥት በግዙፉ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ትዊተር ላይ ይፋዊ ቅሬታውን ያቀረበው ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚሰጡ ድምጾችን እያፈነ ነው በሚል መሆኑን አስታውቋል፡፡

ይህንኑ የገለጹት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቃል አቀባይ ቢልለኔ ሥዩም፣ ኩባንያው ለኢትዮጵያ ድጋፍ የሚሰጡ ድምጾች እየታፈኑ ነው ያሉ ሲሆን፣ በአንጻሩ ሕወሓትን የሚደግፉና የመንግሥት ለውጥ እንዲካሄድ የሚቀሰቅሱ ሐሳቦች እንዲጸባረቁ ይፈቀዳል ብለዋል፡፡

‹‹በሕወሓት እና በሕወሓት ደጋፊዎች ኢትዮጵያን የተመለከቱ ሐሰተኛ ዜናዎች መሰራጨታቸውን ቀጥለዋል›› ያሉት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ፣ የሕወሓት አባላት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግሥት በኃይል ለመጣል በይፋ ጥረት እያደረጉ ነው ሲሉ ከሰዋል፡፡

ቢልለኔ ‹‹እነዚሁ ግለሰቦች ከቀድሞ እና ከአሁን ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ጋር መንግሥትን ለመጣል ሲያሴሩ የሚያሳይ ሾልኮ የወጣ ተንቀሳቃሽ ምስል ታይቷል›› በማለት በአስረጂነት ከሰሞኑ በስፋት መነጋገሪያ የነበረውን በሰላም እና ልማት ማእከል ተዘጋጅቷል የተባለውን የውይይት ቪዲዮ ጠቅሰዋል።

በመንግሥት ቅሬታ የቀረበበት ትዊተር፣ ከሰሞኑ በተመሳሳይ ‹ኖ ሞር› የሚል ሥያሜ ዘመቻ የሚያደርጉ አካውንቶችን አግዷል በሚል ቅሬታዎች ሲቀርብበት ተስተውሏል፡፡

ትዊተር ባለፉት ቀነት «ኖ ሞር» የተሰኘውን ይህንኑ ዘመቻ በዋነኝነት ያስተባብራል የተባለውንና የኤርትራ መንግሥት የቅርብ ሰው የሆነውን ስምኦን ተስፋማርያም እና እሱ የሚመራውን ሆርን ኦፍ አፍሪካ ሀብ እና ኒው አፍሪካ ኢንስቲትዩት የተባሉ የትዊተር አካውንቶችን ማገዱን አሳውቋል፡፡

ይህንኑ ተከትሎም የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የማነ ገብረመስቀል፣ እግዱ አግባብ አይደለም በማለት ተቃውመው ጽፈዋል፡፡

ነገር ግን ትዊተር ኩባንያ የግለሰቡን አካውንት ያገድኩት ደንብ በመጣሱ ነው ያለ ሲሆን፣ ተጥሰዋል ካላቸው ደንቦች መካከል ሐሰተኛ አካውንቶችን በመጠቀም ተመሳሳይ ይዘቶችን በብዛት ከአንድ ቦታ በተለያዩ አካውንቶች ማሰራጨት የሚል መጥቀሱን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል፡፡

በመንግሥት ቅሬታ የተሰነዘረበት ትዊተር ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ያለ ሲሆን፣ ግጭት ቀስቃሽ እና ሰዎችን ዝቅ የሚያደርጉ ይዘቶችን እንደማያስተናግድ ገልጾ ነበር።

በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ በተለይ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን የበርካቶችን ትኩረት ያገኙ ርዕሶችን ማሳየት አቁሟል። ትዊተር የአሁኑን ዓይነት ካውንቶችን የመዘጋት እርምጃ ሲወስድ ከቅርብ ጊዜህ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img