አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ኅዳር 21፣ 2014 ― ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሕወሓት ኃይሎችን በሙሉ እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ከባለፈው ሳምንት አንስቶ የአገር መከላከያ ሠራዊትን በጦር ግንባር በመገኘት እየመሩ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኸው ጥሪያቸው በመንግስት መገናኛ ብዙኃን ተላልፏል።
ከሕወሓት ጋር ተሰልፈው የሚገኙ ተዋጊዎች ለመከላከያ፣ ለክልል ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ እጃቸውን በመስጠት ራሳቸውን እንዲያተርፉ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “የትግራይ ወላጆችም ልጆቻችን የት ደረሱ” ብለው ይጠይቁ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርነቱ በሚካሄድበት በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚገኙ የጦር ግንባሮች መካከል በአንደኛው ተገኝተው የዘመቻ የመጨረሻ ዕቅድ ላይ እንደመከሩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በማኅበራዊ ገጹ ላይ አመልክቷል።
የሕወሓት ኃይሎች በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የሚካሄደው ዘመቻ በአጭር ጊዜ እና በአነስተኛ መስዋዕትነት ድል የሚረጋገጥበትን መመሪያ መስጠታቸውን አስታወቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የኢትዮጵያ ፍላጎት ሰላምና ልማት ነው። ወደእዚህ ጦርነት የገባነው ተገድደን ነው። ማሸነፋችን ግን አይቀሬ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።