Saturday, November 23, 2024
spot_img

በሱዳን በኩል ሰርገው የገቡ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን መንግሥት አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ኅዳር 20፣ 2014 ― በሱዳን በኩል ሰርገው የገቡ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር በዛሬው እለት አስታውቋል፡፡

የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዲኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ ታጣቂዎቹ ‹‹የጥፋት ኃይል›› ካሉት ሕወሓት ጋር የተገናኙ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የሱዳን ዜና ወኪል የሆነው ሱና የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በአልፋሽቃ አካባቢ በተሰማራው የሱዳን ሠራዊት ላይ የኢትዮጵያ ጦርና ሚሊሻ ጥቃት ፈጽመዋል ብሏል።

ነገር ግን ወይዘሮ ሰላማዊት ካሳ የሱዳን ወታደሮች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል በሚል አንዳንድ ዘገባዎች ቢኖሩም፣ ፍጹም ሐሰት ነው ብለውታል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታው አያይዘውም በሱዳን በኩል ተወሮ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ግዛት በተመለከተ መንግስት ከሱዳን ጋር ያለውን የዘመናት አብሮነት እና ትስስር መሠረት ባደረገ መንገድ መፍትሔ እፈላለገ ይገኛል ሲሉ አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም የአገራቱን ግንኙነት ለመበረዝ ታልመው የሚሠሩ ዘገባዎች መኖራቸውን በመጥቀስ፣ ይህ ተጽእኖ እንደማያሳርፍ ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ዘገባ ከሠሩት መካከል ሬውተርስ የዜና ወኪል በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ ቅዳሜ ዕለት ተፈጸመ በተባለው ጥቃት ስድስት የሱዳን ወታደሮች ተገድለዋል ብሏል፡፡

ነገር ግን የኢፌዴሪ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ከሱዳን በኩል የቀረበውን ክስ በማጣጣል፣ ‹‹ኢትዮጵያ ጥቃት የምትፈጽምበት ምክንያት የለም›› ሲሉ ለኢሳት ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ አገራት መካከል የድንበር ውዝግብ እንዳለ ያስታወሱት ጄነራል ብርሃኑ ጁላ፣ ይህ በሕጋዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት ኢትዮጵያ ጽኑ አቋም እንዳላት አመልክተው ‹‹መሬታችን በሰላም፣ በሕግና በድርድር ይመለሳል ብለን ስለምናስብ፣ በዚህ ወቅት ሱዳንን የምናጠቃበት ሁኔታ ላይ አይደለንም›› ብለዋል።

ከዚህ በተቃራኒው ከሱዳን በኩል የመተናኮል ምልክቶች እየታዩ መሆናቸውን የጠቀሱት ኤታማጆር ሹሙ፣ ከሱዳን በኩል ታጣቂዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ እንደሚደረግና ‹‹የሕዳሴው ግድብ ግንባትን ለማደናቀፍ እየሰራች መሆኑን እናውቃለን›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ‹‹እነሱ የላኳቸው ኃይሎች እየመጡ እየደመሰስናቸው ነው። የራሳችንን ተላላኪዎች መደምሰስ እንጂ ለምን ትልካላችሁ ብለን ከእነሱ ጋር ውዝግብ፣ ግጭትም ሆነ ጦርነት ውስጥ መግባት አንፈልግም›› ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ሱዳን አል ፋሻቃ በሚባለው ለም መሬት አካባቢ ለረዥም ጊዜ የቆየ ውዝግብ ውስጥ እንዳሉ የሚታወቅ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img