አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሚያዝያ 18፣ 2013 ― ግንባታቸው ከተጠናቀቁ ሁለቱ የሕዳሴ ግድብ ዩኒቶች በነሐሴ ወር 750 ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚመነጭ የገለጹት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ ናቸው፡፡ግንባታቸው የተጠናቀቁት ሁለቱ የግድቡ ዩኒቶች እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አላቸው ነው የተባለው፡፡ እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ በመጀመርያው ዙር ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚመነጨው ኃይል፣ 300 ሜጋ ዋት ከሚያመነጨው ተከዜና 420 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ካለው ግልገል ጊቤ ሁለት የኃይል ማመንጫ ግድቦች የበለጠ የማመንጨት አቅም አለው፡፡በሁለቱ ዩኒቶች ከህዳሴው ግድብ በዓመት 4,000 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ ለማመንጨት የታቀደ ሲሆን፣ ይህም ኃይል በአራት ሺሕ ሚሊዮን ኪሎ ዋት ተባዝቶ የሕዝብ ተደራሽነቱ ሲገለጽ በዓመት ብቻ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡በመጪው ክረምት ኢትዮጵያ ሁለት ትልልቅ አገራዊ ክንውኖችን በህዳሴው ግድብ ላይ የምትተገብር እንደሆነ ያስረዱት አሸብር (ኢንጂነር)፣ ይህም የሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌትና በሁለት ዩኒቶች ኃይል የማመንጨት ዕቅድ ናቸው፡፡የህዳሴው ግድብ በተሻለ አፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ሁለት የውኃ ማስተንፈሻዎች ተጠናቀቀው ሥራ መጀመራቸው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ የግድቡ የሲቪል ሥራ 91 በመቶ፣ እንዲሁም የብረታ ብረት ሥራ 53 ነጥብ 7 በመቶ መከናወናቸውንና በአጠቃላይ የግድቡ ግንባታ 79 በመቶ መድረሱን ጠቁሟል፡፡ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመጀመርያ ዙር እንዲይዝ የታቀደለትን 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በሐምሌ 2012 መያዙ ያስታወሰው ሪፖርተር ነው፡፡