አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ኅዳር 19፣ 2014 ― ከ33 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ66 ቅርንጫፎች የሚሠሩ 422 ሠራተኞቹን በደንብ ጥሰት ጠርጥሮ ማገዱ ተነግሯል።
ዕግዱ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ለሠራተኞቹ ያልተገለጸ ሲሆን፣ ተግባራዊ የሆነው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች መታገድ፣ በባንኩም ሆነ በዘርፉ የተለመደ እንዳልሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ የሠራተኞቹ የኅዳር ወር ደመወዝም መታገዱንም ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
ሠራተኞቹ የታገዱት ባንኩ ላልፈቀደው ሌተር ኦፍ ክሬዲት የመርከብ ጭነት ክፍያ ለደንበኞች በመፈጸም በመጠርጠራቸው መሆኑ ተጠቁሟል።
አንዳንድ ሠራተኞች ደግሞ ዳያስፖራ አካውንት ለከፈቱ ደንበኞች፣ ከተገልጋዮቹ የውጭ ምንዛሪ ሒሳብ በመቀነስ፣ የመርከብ አገልግሎት ክፍያዎችን መፈጸም ቢኖርባቸውም፣ በተቃራኒው በብር አስገብተው ባንኩ በዶላር እንዲከፍል በማድረግ በመጠርጠራቸው እንደሆነ ጋዜጣው ሥማቸውን ያልጠቀሳቸውን ኃላፊዎች ጠቅሶ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰኔ 17፣ 2002 ያወጣውን መመርያ በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማናቸውም በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ተጭነው ለሚገቡ የገቢ ዕቃዎች የሚከፈል የጭነት ክፍያ፣ በውጭ ምንዛሪ እንዲሆን በተመሳሳይ ወቅት ለሠራተኞቹ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።
ሠራተኞችም የውጭ ምንዛሪውን ተመጣጣኝ ገንዘብ ከደንበኞች ላይ በመሰብሰብ፣ በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት ስም በተከፈተው ሒሳብ ገቢ እንዲያደርጉና ድርጅቱ ወደሚፈልገው አገር ባንክ በውጭ ምንዛሪ እንዲያስተላልፉ ታዘው ነበር።
ነገር ግን የጭነት ክፍያዎችን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መፈጸም የሚችሉት፣ በባንኩ በኩል ከውጭ ዕቃ እንዲያስመጡ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑ ተጠቁሟል።
ከ60 ሺሕ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች ያሉት ንግድ ባንክ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመርያ ሦስት ወራት 6.8 ቢሊየን ብር ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን፣ 30.5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አግኝቷል። ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ትርፉ የ122 በመቶ ዕድገት ሲያሳይ ገቢው በ92 በመቶ አድጓል።