Monday, October 7, 2024
spot_img

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እዝ ‹‹የሐሳብ ነጻነትን ሰበብ በማድረግ›› ሕወሓትን ልዩ ልዩ ሚዲያ በመጠቀም ለሚደግፉ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ኅዳር 17 2014 ― የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እዝ ‹‹የሐሳብ ነጻነትን ሰበብ በማድረግ›› ልዩ ልዩ የሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም፣ ሕወሓትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በመደገፍ ‹‹በህልውና ዘመቻው ላይ ዕንቅፋት የሚፈጥሩ አካላት›› ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋል፡፡

እዙ ይሄን ማስጠንቀቂያ ተላልፈው ከድርጊታቸው በማይቆጠቡ አካላት ላይ የጸጥታ ኃይሎች ተገቢውን ርምጃ እንዲወስዱ መታዘዙንም አስታውቋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እዙ ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ማንኛውም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን፣ የጦር ሜዳ ውሎዎችንና ውጤቶችን በተመለከተ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ሥልጣን ከተሰጠው አካል ውጪ፣ በየትኛውም የመገናኛ አውታር መስጠትና ማሰራጨት ክልክል መሆኑንም እወቁት ብሏል።

በሌላ በኩል እዙ የመከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስን ጨምሮ በማንኛውም ሁኔታ የመለዮ ለባሾን ዩኒፎርም ለብሶ መገኘትን ከልክሏል፡፡

የመለዮ ለባሾች ዩኒፎርም የራሱ የሆነ የአለባበስ ሕግና ሥርዓት እንዳለው የገለጸው እዙ፣ ከዚህ ሕግና ሥርዓት ውጭ የመለዮ ለባሾችን ዩኒፎርም ለብሶ መገኘት የተልእኮ አፈጻጸሙን እያወከ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡

በመሆኑም በማንኛውም ሁኔታ፣ ቦታና ጊዜ የመከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስን ጨምሮ የክልል ልዩ ኃይሎችንና የመደበኛ ፖሊስን ዩኒፎርሞች፣ የጸጥታ አካላት አባል ያልሆነ ማንኛውም ሰው ለብሶ መገኘት ፈጽሞ የተከለከለ ሲሆን፣ የተቋማቱ አባል ሳይሆንና የታደሰ መታወቂያ ሳይዝ ዩኒፎርሙን ለብሶ በተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ፣ የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ ታዟል።

በዚሁ መግለጫ ላይ ‹‹በሀገራችን ህልውና ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመቀልበስ መንግሥትና ሕዝብ ተቀናጀተው ወቅታዊና ሕጋዊ ርምጃን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ›› ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እዝ፣ ‹‹ሆኖም ይሄን አጋጣሚ በመጠቀም፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ከሚፈቅደው ውጪ የሽግግር መንግሥት ወይም ሌላ ሕገ ወጥ ቅርጽ ያለው መንግሥት እንመሠርታለን ብለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ አካላት ላይ የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ›› መታዘዙን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img