Sunday, October 6, 2024
spot_img

በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ከተማዋ የተረጋጋች በመሆኗ የተለመደ ሥራችንን ቀጥለናል አለ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 16፣ 2014 ― በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ከተማዋ የተረጋጋች በመሆኗ የተለመደ ሥራችንን ቀጥለናል ሲል አስታውቋል፡፡

ኤምባሲው በአዲስ አበባ ከተማ ያለው ሁኔታ የተረጋጋ በመሆኑ ሠራተኞቹንና ቤተሰቦቻቸውን የማስወጣት ዕቅድ እንደሌለውም ነው ያስታወቀው፡፡

የኤምባሲው ፕሬስ አገልግሎት በይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መግለጫው፣ በመላው አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባለው የዕለት ተለት እንቅስቃሴ ላይ የጎላ ለውጥ እንዳልታየ አመልክቷል።

ኤምባሲው ጨምሮም በከተማዋ ውስጥ ባሉ የመንግሥት ሕንጻዎች፣ የአየር ማረፊያና በመሳሰሉት ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት አካባቢ የተጠናከረ የደኅንነት ጥበቃ እንዲሁም በጎዳናዎች ላይ ቅኝት እንደሚደረግ ጠቅሷል።

አያይዞም የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተለመደ ሥራውን እያከናወነ መሆኑን የጠቀሰው ኤምባሲው፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በቅርቡ እንዳለው በአገሪቱ ውስጥ የሚደረጉ በረራዎች ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑንም አስታውሷል።

ነገር ግን ኤምባሲው ለአስቸኳይ ጉዳይ አስፈላጊ ሆኖ አስካላገኙት ድረስ የሩሲያ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

በቅርብ ቀናት ተባብሶ መቀጠሉ በሚነገርለት የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓት ኃይሎች ጦርነት፣ አሜሪካን ጨምሮ የተወሰኑ አገራት ዜጎቻቸውና ዲፕሎማቶቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸው መነገሩ አይዘነጋም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀነዓ ያደታ በበኩላቸው በከተማዋና ዙሪያዋ አስተማማኝ ሰላም እንዳለ በመግለጽ፣ ለዚህም የከተማው የፀጥታ ኃይል ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከሪፐብሊካን ዘብ፣ ከኦሮሚያ ፖሊስ እና ከሌሎች የፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ጋር በመሆን በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img