አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 15፣ 2014 ― በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብና የግብርና ድርጅት (ፋኦ) የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት ለአንበጣ መከላከያ ድጋፍ ሰጥቶ የነበረውን ሔሊኮፕተሮች እንዳያበር መከልከሉ ተሰምቷል።
ድርጅቱ ሔሊኮፕተሮቹ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ መታወጁን ተከትሎ እንዳይበሩ ማድረጉን ሪፖርተር ጋዜጣ ከአንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን አረጋግጫለሁ ብሎ ዘግቧል።
ለተመሳሳይ ተግባር በግብርና ሚኒስቴር ግዥያቸውን ለመፈጸም በሒደት ላይ የነበሩ ሔሊኮፕተሮችና ድሮኖች፣ የዓለም ባንክ ለሌላ ዓላማ ሊውሉ ይችላሉ በሚል ምክንያት ብድሩን ማጓተቱም ተነግሯል።
ሆኖም በኢትዮጵያ የምግብና ግብርና ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ታምሩ ለገሰን ስለክልከላው ጠይቄ መረጃ የለኝይም እንዳሉት ጋዜጣው አስነብቧል።
ኃላፊው ‹‹ለአንበጣ አሰሳና ለኬሚካል መርጫ የሰጠናቸው ሔሊኮፕተሮች እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሲሠሩ እንደነበረ አውቃለሁ። ከአዋጁ ጋር ተያይዞ ቆመው ከሆነ ከአለቆቼ አረጋግጬ እመልሳለሁ›› ማለታቸው ተመላክቷል።
ድርጅቱ ሔሊኮፕተሮችን ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ካሉ ትልልቅ የግል እርሻ ባለቤቶች በማስመጣት ኪራያቸውንና ነዳጅ እየቻለ፣ በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ ለተቋቋመው የአንበጣ መከላከል ግብረ ኃይል ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር ነው የተነገረው።
ለሦስት ዓመታት ምሥራቅ አፍሪካን ሲያምስ የነበረው የበረሃ አንበጣ የመዛመት ፍጥነቱ በአሁኑ ጊዜ የተገታ ቢመስልም፣ በማንኛውም ወቅት ተመልሶ ዕፅዋትና ሰብል ሊያወድም እንደሚችል ሥጋታቸው የሚያጋሩ አሉ።
‹‹አገራዊ አቅም እየገነባን ነበረ። ነገር ግን ብዙ የውጭ ጫና እየተደረገብን ነው›› ሲሉ ስማቸው ያልተጠቀሰው ባለሥልጣን ገልጸዋል።