Wednesday, November 27, 2024
spot_img

የቶሚ ሄልፊገር እና ካልቪን ክሌይን አምራቹ የአሜሪካ ድርጅት ከወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በሐዋሳ የሚገኘው ድርጅቱን ሊዘጋ መሆኑ ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ኅዳር 10 2014 ― ቶሚ ሄልፊገር እና ካልቪን ክሌይንን ጨምሮ ሌሎች የታወቁ የምርት ሥሞች ባለቤት የሆነው የአሜሪካው የልብስ አምራች ፒቪኤች ኮርፕ፣ ከወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በሐዋሳ ኢንዱትሪያል ፓርክ የሚገኘው ድርጅቱን ሊዘጋ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የልብስ አምራቹ ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ሳራ ክላርክ ይህንኑ ረቡእ ኅዳር 8፣ 2014 ማስታወቃቸውን ቢዝነስ ኦፍ ፋሽን የተሰኘ ድረ ገጽ ዘግቧል፡፡

ሳራ ክላርክ ድርጅቱ ውሳኔውን ለማሳለፉ በፍጥነት እየተለዋወጠ ነው ያሉት የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ ከሽያጭ ጋር የተገናኘ ነገሮችን አስቸጋሪ ማድረጉን መናገራቸው ተጠቅሷል፡፡

ድርጅቱ አሁን ሥራዬን ላቆም ነው ቢልም፣ ወደፊት ሥራውን በሚያስቀጥልበት ሁኔታ ላይ የረዥም ጊዜ የመፍትሔ አማራጮችን ማሰሳችን አይቀርም ማለታቸውም በዘገባው ተመላክቷል፡፡

ድርጅቱ መሠረቱን ያደረገባት አሜሪካ፣ ከሰሞኑ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል በኢትዮጵያ ያሉ ዜጎቹ በአስቸኳይ እንዲወጡ ማሳሰቧ ይታወሳል፡፡ አገሪቱ ዜጎቿ እንዲወጡ የጠየቀችው በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት መባባሱን ተከትሎ ነው፡፡

አሜሪካ ከዚህ በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የሚነሱ እና የሚያርፉ አውሮፕላኖችን አብራሪዎችን አስጠንቅቃለች፡፡ አገሪቱ አብራሪዎቹን ያስጠነቀቀችው በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት ወደ አዲስ አበባ ሲቃረብ አውሮፕላኖች ከሰማይ ላይ ወይም ባረፉበት መሬት ላይ ሆነው ለጥቃት ሊጋለጡ ይችላሉ ስትል ነው፡፡

የአሜሪካ ፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር አማካሪ የሕወሓት ተዋጊዎች ቦንብ የተገጠመላቸው ሮኬቶች፣ ፀረ ታንኮች፣ የአጭር ርቀት ጸረ አውሮፕላን ከባድ መሳሪያዎች እና በሰው የሚንቀሳቀሱ አየር መቃወሚያ የመሳሰሉ ከመሬት 25 ሺሕ ጫማ መምዘግዘግ የሚችሉ ፀረ አውሮፕላን መሳሪያዎች ታጥቀዋል ብለዋል፡፡ አሜሪካ ይህን ማስጠንቀቂያ ብታወጣም፣ ከመንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡

አገሪቱ ቀድሞ ዜጎቿን ይውጡ ማለቷን ተከትሎ ዩናይትድ ኪንግደም እና ሳዑዲ ዐረቢያን ጨምሮ ሌሎችም አገራት በተመሳሳይ ዜጎቻቸው ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ያሳሰቡ ቢሆንም፣ መንግሥት ግን አገራት ያስተለላለፉት ማሳሰቢያ የተጋነነ ነው ሲል አጣጥሎታል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img