አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 8፣ 2014 ― ከዓለማችን ግዙፍ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች መካከል የሆነው ትዊተር፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ አሁንም ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ሲል በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ የተጠቃሚዎቹን እና መሬት ላይ ያሉ ሰዎችን ደህንነት መጠበቅ ቀዳሚ ትኩረቱ መሆኑን የገለጸው ኩባንያው፣ የሚለቀቁ የመረጃዎችን ደህንነት ማስጠበቅ ላይ እየሠራ ስለመሆኑም ነው የገለጸው፡፡
ኩባንያው በመግለጫው ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተለዋዋጭ መሆኑን በማስታወስ፣ በገጹ የሚጋሩ አንዳንድ ይዘቶች መሬት ላይ የወረደ ተጨባጭ ተጽዕኖዎች እንዳላቸው አስታውቋል፡፡
እንዲህ ዐይነት ጎጂ ተጽዕኖ ያላቸውን ይዘቶች ያን ያህል ጎልተው እንዳይታዩ እንደሚያደርግም ነው ኩባንያው ያመለከተው፡፡
በድርጊቶች ላይ ተመስርቶ መሬት ላይ ያለውን ጉዳት ከግምት ውስጥ ያስገቡ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ያስጠኘቀቀው ትዊተር፣ በኢትዮጵያ በዋናነት አነጋጋሪ ጉዳዮች የሚንሸራሸሩበትን አምድ ወይም ትሬንድ፣ መልዕክቶችን ለማጋራትና ለመጋራት የሚቻልባቸውን የቡድንና ሌሎች ዝርዝሮችን እና ማስታወቂያዎችን ማቆሙን በማስታወቅ ደህንነቱ የተጠበቀ ፍለጋ ለማድረግ የሚያስችል አዲስ አገልግሎት መጀመሩንም አስታውቋል፡፡
ይህን ለመወሰን ታማኝ ካላቸው የተለያዩ የሃገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አጋር ተቋማትና ባለሞያዎች ጋር በመነጋገር እርምጃውን እንደወሰደ አስፍሯል፡፡