አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 8፣ 2014 ― አንድ ዓመት ባስቆጠረው የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓት ጦርነት ሰበብ ጎረቤት አገር ጂቡቲ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ማጣቷን የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ኢልያስ ሙሳ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት አገራቸው 1.7 ቢሊዮን ዶላር ወይም ግማሽ ያህል ብሔራዊ ሐብቷን ያጣችው ገቢ በመቀነሱ እና ሥራዎች በመጥፋታቸው መሆኑን እንደነገሩት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ፣ ‹‹አሁን የሚያሳስበን የ20 ዓመታት ጠንካራ ሥራ እንዲሁም ከኢትዮጵያ እስከ ጂቡቲ ያለው የቀጠናው ልማት ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ይህም የተከሰተው በዚያ ግጭት መነሻ ምክንያት ነው። ጂቡቲ ሁሌም ለሰላም አፅንኦት ትሰጣለች። ቀጣናውም ሆነ ጂቡቲ ይህን ጦርነት አይችሉትም›› ማለታቸውም በዘገባው ተመላክቷል፡፡
አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ጂቡቲ፣ የተለያዩ ችግሮችን እየተጋፈጠች መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ በጦርነት የሚመጣ ዳፋ ተጨማሪ ተግዳሮት መሆን የለበትም ብለዋል፡፡
ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የሸቀጥ ዕቃ በጂቡቲ ወደብ በኩል የሚያልፉ ሲሆን፣ ይህ ለአገሪቱ ከ1 ነጥብ 5 እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኝላታል ነው የተባለው፡፡