Sunday, September 22, 2024
spot_img

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከሰሞኑ ዳግም ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 7፣ 2014 ― ባለፈው እሑድ አዲስ አበባ የነበሩት የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ዳግም ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋሺንግተን ፖስት ዘግቧል።

ፕሬዝዳንቱ ወደ አዲስ አበባ የሚያቀኑት በአሁኑ ጊዜ አገራቸው የሚገኙት የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ እንደሚሆን ነው ዘገባው የጠቆመው።

የፕሬዝዳንት ኬንያታ ጽሕፈት ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ ኬንያታ እና ብሊንክን በቀጠናዊ ግጭቶች ዙሪያ እንደመከሩ ከመግለጽ ውጭ ስለ ትግራዩ ግጭት መነጋገራቸውን ለይቶ አልጠቀሰም።

ነገር ግን ብሊንክን ከኬንያ አቻቸው ሪቸል ኦማሞ ጋር በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በትግራዩ ግጭት መፍትሄ በመፈለግ ዙሪያ ከኬንያታ ጋር መወያየታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፣ ኬንያታ ለግጭቱ መፍትሄ ለመፈለግ እያደረጉት ያለውን ጥረትም እንደሚያደንቁ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ አክለው የኢትዮጵያ ጉዳይ ኬንያ እና ሀገራቸውን እኩል በጥልቅ የሚያሳስብ እንደሆነ ተናግረዋል።

አያይዘውም ውጊያው ባለፈው አመት በትግራይ ኋላም በአማራ ክልል ሲስፋፋ በአገሪቱ ዜጎች ለችግር መዳረጋቸውን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል። 

ግጭቱ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ጸጥታ ጭምር ስጋት እንደሆነ የገለጹት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ሁሉም ወገኖች ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ብሊንክን ጦርነቱ እንዲቆም ተፋላሚ አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ሲሰበሰቡ፣ የሰብአዊ እርዳታ በነጻነት ሲሰራጭ፣ የታሰሩ ሰዎች ሲፈቱ፣ ሁሉም ወገኖች ልዩነቶቻቸውን በሰላም እና ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ሲረባረብ ማየት እንፈልጋለን ሲሉ የሀገራቸውን አቋም አስረድተዋል። 

አሜሪካ ለትግራዩ ጦርነት መፍትሔ ለመፈለግ በሚል የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛዋ ጄፍሪ ፌልትማንን ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ ልካ እንደነበር ይታወቃል። ፌልትማን ከኢትዮጵያ በተጨማሪ አሁን ብሊንክንን እያስተናገደች ያለችው ኬንያንም ጎብኝተዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img