አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ኅዳር 7፣ 2014 ― በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሠረት መታወቂያ ሳይዙ መንቀሳቀስ ከ3 እስከ 10 ዓመት እንደሚያስቀጣ ያስታወቀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ነው፡፡
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ በመታወቂያ አሰጣጥ ላይ በዛሬው እለት ውይይት አድርጓል።
በዚሁ ውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀንአ ያዴታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሰረት በማድረግ የጊዜያዊ መታወቂያ አሰጣጥ መመሪያ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
እንደ ኃላፊው፣ መመሪያው ሰላማዊ እና ፀረ ሰላም ኃይሎችን ለመለየት፣ የሐሰት መታወቂያ የሚሰጡ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ለመለየት እንዲሁም የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ሆነው ያለ አግባብ ጊዜያዊ መታወቂያ የሚሰጡትን ለመቆጣጠር የሚያግዝ ነው፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት መታወቂያ ሳይዙ መንቀሳቀስ ከ3 እስከ 10 ዓመት ያስቀጣል ያሉት ኃላፊው፣ ከኅዳር 6፣ 2014 በጀመረውና እስከ ኅዳር 15፣ 2014 በሚቆየው የጊዜያዊ መታወቂያ አሰጣጥ ሂደት ማህበረሰቡ መታወቂያ ማውጣት እንዳለበት መግለጻቸውን ዋልታ ዘግቧል፡፡
የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 መሠረት በከተሞች አካባቢ የነዋሪነት መታወቂያ፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የሰራተኛ መታወቂያ፣ ፓስርፖርት ወይም ከነዚህ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ መታወቂያ ጊዜአዊም ቢሆን ሳይዙ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑ ይታወቃል፡፡