Sunday, September 22, 2024
spot_img

በሕወሓት በተያዙ የአማራ አካባቢዎች ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እርዳታ አለመቅረቡን የክልሉ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ገለጸ

 

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ኅዳር 7፣ 2014 ― በሕወሓት ተይዘው ወራት ባስቆጠሩ የአማራ አካባቢዎች ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እርዳታ አለመቅረቡን የክልሉ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ገልጧል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ እያሱ መስፍን፣ የሰብዓዊ እርዳታ ባለመድረሱ የሰሜን ወሎ፣ ዋግ ኽምራ እና ሌሎች አካባቢዎች በመድኃኒትና በምግብ እጥረት የሰዎች ሕይወት እያለፈ መሆኑን እንደነገሩት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ኃላፊው ዓለም አቀፍ ረጂዎች በገቡት ቃል መሠረት የፌደራል መንግሥትም ሆነ የክልሉ መንግሥት በህወሓት በተያዙ ቦታዎች ላሉ ዜጎቻችን እርዳታ እንዲደረግ ቢነጋገሩም ‹‹ጠብ ያለ ነገር የለም›› ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ እያሱ አያይዘውም በሰብዓዊ እርዳታ እጥረት ንጹሃን እየተጎዱ መሆኑን እና በዋግ ኽምራ ውስጥ 11 ሰዎች በምግብ እና በመድኃኒት እጦት ሕይወታቸው ማለፉን መናገራቸው ተመላክቷል፡፡

እንደ አቶ እያሱ የዓለም ምግብ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርባላሁ ባለባቸው ቦታዎች የሰብዓዊ እርዳታ የሚያቀርበው የተለየ ድርጅት፣ ትራንስፖርት የሚሰራው እና ደኅንነት ላይ የሚሰራ የተለያዩ ድርጅቶች በመሆናቸው ‹‹አንዱ በአንዱ ላይ ምክንያት እየፈጠረ እስካሁን እርዳታ ተደራሽ አልተደረገም›› በማለት ያስረዳሉ።

በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ሰዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ እያሱ፤ እስካሁን 2.1 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

በሕወሓት ቁጥጥር ሥር ባሉ አካባቢዎች 5 ሚሊዮን ሕዝብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው የሚናገሩት አቶ እያሱ፤ በአማራ ክልል ‹የደሃ ደሃ› ተብለው ዕለታዊ የምግብ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው 1.89 ሚሊዮን ተረጂዎች እንደሚገኙም አስታውሰዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img