Sunday, September 22, 2024
spot_img

የሲዳማ እና የደቡብ ክልል አሁንም ድረስ ከተሽከርካሪ በስተቀር የንብረት ክፍፍል አላደረጉም ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ኅዳር 3 2014 ― በ2012 ኅዳር ወር በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ የኢትዮጵያ አስረኛው ክልል የሆነው የሲዳማ ክልል አሁንም ድረስ ከተሽከርካሪ በስተቀር ቀድሞ ከነበረበት የደቡብ ክልል ጋር የንብረት ክፍፍል አለማድረጉ ተነግሯል፡፡

አስረኛው የሲዳማ ክልል እና የደቡብ ክልል እስካሁን የንብረት ክፍፍል አለማድረጋቸው ከሰሞኑ ከሌላኛው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጋር የሥልጣን ርክክብ በተደረገበት የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተነስቷል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የሲዳማ ክልል ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፊሊጶስ ናሆም እንዳረጋገጡለት ኢትዮጵያ ኢንሳይደር በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

እንደ አቶ ፊሊጶስ ከሆነ ይህ የተደረገው አዲሱ የሲዳማ ክልል በሚዋቀርበት ጊዜ አንገብጋቢ የነበረው የተሸከርካሪ ጉዳይ በመሆኑ ምክንያት የተሸከርካሪዎች ክፍፍል በአፋጣኝ ተከናውኗል፡፡ አስረኛው የአገሪቱ ክልል ሲዳማ ከነበረበት የደቡብ ክልል ጋር የሥልጣን ርክክብ ያደረገው በሰኔ 2012 ነበር፡፡

በሲዳማ እና በደቡብ ክልል መካከል የሐብት ክፍፍሉ በወቅቱ አለመጠናቀቁ፤ ነባሩ የደቡብ ክልል አሁን ያለው ንብረት ለሦስት እንዲከፈል እንደሚያደርገውም ነው የተነገረው፡፡ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ይህንኑ በማስመለከት አዲስ የውሳኔ ሐሳብ አጽድቋል፡፡ በውሳኔ ሐሳቡ መሠረት ለሲዳማ ክልል ተጠናቀቅው ከተላለፉት ሐብት እና ዕዳዎች ውጭ ያሉ ያልተጠናቀቁ የጋራ ሀብት እና ዕዳ ክፍፍል የደቡብ፣ የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በጋራ በተገኙበት ይከናወናል፡፡

በመስከረም ወር መገባደጃ የሕዝበ ውሳኔ ያደረገው አስራ አንደኛ ሆኖ የተመዘገበው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ በተመሳሳይ ጥቅምት 24፤ 2014 በተካሄደው የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሥልጣን ርክክብ አድርጓል፡፡

አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሐብት እና ዕዳ ክፍፍልን በተመለከተ በፍጥነት የተሸከርካሪ እና የበጀት ክፍፍል የማድረግ ውጥን መያዙን የክልሉ አደራጅ ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ ምትኩ ታምሩ ለድረ ገጹ ተናግረዋል፡፡

አስራ አንደኛውን የኢትዮጵያ ክልል የመሰረቱት የካፋ፣ ቤንች ሸኮ፣ ሸካ፣ ዳውሮ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img