Wednesday, November 27, 2024
spot_img

ብሔራዊ ባንክ ለጫት ላኪዎች ብድር ፈቀደ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ኅዳር 2 2014 ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጫት መላክ ላይ ለተሰማሩ ነጋዴዎች ብድር እንዲፈቅዱ ለባንኮች ትዕዛዝ አስተላልፏል፡

የዛሬ ሦስት ወር ገደማ ተንቀሳቃሽ ያልሆኑ ንብረቶችን በመያዝ ብድር መስጠት መከልከሉን ተከትሎ ባንኩ ለተለያዩ ዘርፎች ዕገዳውን ያነሳ ቢሆንም ለጫት ላኪዎች ሳይነሳ መቆየቱን ያስታወሰው ሪፖርተር ጋዜጣ፣ ዘርፉ የሚያስገኘውን የውጭ ምንዛሪ ከግምት ውስጥ በማስገባት ዕግዱ መነሳቱን የብሔራዊ ባንክ የባንክ ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው ነግረውኛል ብሎ ዘግቧል፡፡

 መንግሥት ቀድሞ የጣለውን የብድር ዕገዳ ‹‹የኢኮኖሚ አሻጥርን›› ለማስቀረት ያለመ ነው ቢልም፣ የንግድ ማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ዘገባው አመልክቷል፡፡

በዕግዱ የተካተቱት ጫት ላኪዎች ቅሬታቸውን ለብሔራዊ ባንክና ለባንኮች ሲያሰሙ ቆይተዋል ነው የተባለው።

ዓምና ከተላከው 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ምርቶች ውስጥ የጫት ድርሻ ወደ 11 በመቶ ሲሆን፣ ይህም እንደ ሰሊጥ ካሉ የቅባት እህሎች ከተገኘው ገቢ የላቀ ነው።

የእግዱን መነሳት በተመለከተ ለዘርፉ ተዋናዮች ብድር መፍቀዱን ያደነቁት የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት ተፈሪ መኮንን፣ ዕርምጃው ላኪዎችን ከማገዝ ባለፈ ለኢኮኖሚው ይዞት የሚመጣው ጥቅም ቀላል እንደማይሆን ገልጸዋል፡፡

የጫት ላኪዎች ከባንክ የሚወስዱትን ብድር ጫት ከገበሬዎች በሚሰበሰቡበት ወቅት ለመክፈልና ጫት ለሚቀነጥሱ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው የቀን ሠራተኞች ደመወዝ እንደሚያውሉት በዘርፉ የተሰማሩ ያነሳሉ።

አሁን ብድር መፈቀዱንም ለሥራ ማስኬጃ የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ከመሸፈን አኳያ ትልቅ ሚና እንዳለው በዘርፉ የተሰማሩ መናገራቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img