አምባ ዲጂታል፣ረቡዕ ኅዳር 1፣ 2014 ― ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትሳፕን የያዘው ግዙፉ ሜታ ኩባንያ ከባፈው ዓመት ግንቦት ወር አንስቶ እስከ ጥቅምት ወር ድረስ ኢትዮጵያን በሚመለከቱ ከ92 ሺሕ በላይ ይዘቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው እርምጃውን የወሰደባቸው ይዘቶች ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ላይ የተሠራጩ መሆናቸውን ነው የገለጸው፡፡ እርምጃው የተወሰደው የድርጅቱን የጥላቻ ንግግር ደንብን በጣሱት ላይ መሆኑን ያሳወቀው ሜታ፣ 98 በመቶ ያህሉ በሌሎች ሪፖርት ከመደረጉ በፊት እንደተደረሰባቸው ጠቅሷል።
በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ እየተከተታተለ መሆኑን ያመለከተው ኩባንያው፣ ከሁለት ዓመታት በላይ በአገሪቱ ውስጥ ከነበሩት አስከፊ የግጭት ስጋቶች አንጻር የሰዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል አጠቃላይ ስትራቴጂን በመተግበር ላይ እንደቆየም ገልጧል፡፡
ሜታ ኢትዮጵያን ከሁለት ዓመት በፊት ለግጭት እና ለአመጽ ከፍተኛ ተጋላጭ ናቸው ከሚባሉት ምድብ ማሻገሩን ያስታወሰ ሲሆን፣ የተቋሙን ፖሊሲዎች የሚጥሱ ይዘቶችን በማስወገድ፣ የሰዎችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በመደገፍ እንዲሁም ሰዎች ኦንላይንም ሆኑ አልሆኑ ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ትኩረት አድርጎ መስራቱን አክሏል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ብዛት ያላቸው ቋንቋዎች ስለሚገነሩ በሁሉም መስክ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ያሰበውን በሙሉ ማሳካት አዳጋች መሆኑን የጠቆመው ሜታ፣ እርምጃውን ሲወስድ ለግጭቱ ማዕከል ናቸው ባላቸው በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በሶማሊኛ እና በትግርኛ የሚወጡ ይዘቶችን መገምገሙን ነው የገለጸው፡፡
በቅርብ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ጋር በተገናኘ በተደጋጋሚ ስሙ የሚነሳው ሜታ፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ በገጻቸው ላይ ያወጡት ጽሑፍ ግጭት ቀስቃሽ ነው በሚል እንዲነሳ ማድረጉ ይታወሳል።
ኩባንያው በቅርቡ በቀድሞ ሠራተኛው የፍራንሲስ ሐውገን ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎችም አገራት ሐሰተኛ መረጃ እና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን ማስቆም አልቻለም በሚል ወቀሳ ቀርቦበታል፡፡