Saturday, September 21, 2024
spot_img

ልማት ባንክን ለመደገፍ የተዘጋጀው ቦንድ ከወለድ አልባ ባንኮች አሠራር ጋር እንደሚቃረን ተጠቆመ

አምባ ዲጂታል፣ረቡዕ ኅዳር 1፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ለመደገፍ ባንኮች የጥቅል ብድራቸውን አንድ በመቶ ለቦንድ ግዥ እንዲያውሉ የሚያስገድደው መመርያ ከወለድ አልባ ባንኮች አሠራር ጋር እንደሚቃረን ተጠቁሟል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት ተግባራዊ የተደረገውን ቦንድ የመክፈያ ጊዜ ሲደርስ ሦስት በመቶ ወለድ ለባንኮች እንዲከፈል የሚያስገድድ ነው፡ ይህም ወለድ አልባ ባንኮች ከሚከተሉት የሸሪዓ ሕግ ጋር የሚፃረር መሆኑን የዘርፉ ባለሞያዎች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፋይናንስ ኢንዱስትሪውን በ850 ሚሊዮን ብር የተቀላቀለው የዘምዘም ባንክ የስትራቴጂክ ዕቅድ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር አቶ ከድር አባስ ነግረውኛል ብሎ ሪፖርተር ጋዜጣ እንዳስነበበው፣ ወለድ አልባ ባንኮች ወለድ የሚከፍል ቦንድ ግዥ መፈጸም የማይችሉ በመሆኑ ከተፈጠሩበት ዓላማ ጋር የሚቃረን ነው፡፡

በኢትዮጵያ የወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ ከስምንት ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም፣ በመስኮት ደረጃ ተገድቦ የነበረው አገልግሎት ወደ ሙሉ ባንክ አገልግሎት እንዲያድግ ከዛሬ ሦስት ዓመታት አንስቶ መወሰኑን ተከትሎ ለሁለት ባንኮች ፈቃድ ተሰጥቷል።

ከዘምዘም ባንክ በተጨማሪ ሒጅራ ባንክ ከተቀላቀሉት ወለድ አልባ ባንኮች መካከል ሲሆን፣ በ700 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የፋይናንስ ዘርፉን የተቀላቀለው ባለፈው ዓመት ነው። በተመሳሳይ ጋዜጣው ስማቸውን ያልጠቀሳቸው የባንኩ የሥራ ኃላፊ እንደናገሩት፣ የቦንድ ግዥን አስገዳጅ የሚያደርገውን መመርያ ጨምሮ ብሔራዊ ባንክ ሌሎች የፋይናንስ ሕጎችን ከወለድ ነፃ አገልግሎት ሰጪዎች አሠራር አኳያ ሊፈተሽ ይገባል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በቦንድ ፈንታ የወለድ አልባ ባንኮች ልማት ባንክን ሊደግፉ የሚችሉበት አማራጭ እንዳለ የየሚናገሩት ኃላፊው፣ ለአብነት ሙዳራባህ የተሰኘውን የወለድ ባንክ አገልግሎት ዓይነት በማንሳት ወለድ አልባ ባንኮች ተበዳሪው ሊያከናውን ያሰበው ፕሮጀክት ላይ ትርፍ ተጋሪ በመሆን ፋይናንስ ማቅረብ እንዲችሉ እንደሚስችላቸው ገልጸዋል፡፡

የዘምዘም ባንክ ዳይሬክተሩም ይህ በሚደረግበት ጊዜ ተበዳሪው የሚሠራው ፕሮጀክት ከሸሪዓ ሕግ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል ያሉ ሲሆን፣ ልማት ባንክም የወለድ አልባ ፋይናንስ የሚያቀርብበት ራሱን የቻለ ክፍል ሊያቋቁም እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ቺፍ ኢኮኖሚስት ፈቃዱ ድጋፌ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች በወለድ አልባ ባንኮች በኩል የቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብ በማጤን ላይ መሆናቸውን በመጠቆም፣ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img