Sunday, September 22, 2024
spot_img

የቀድሞዋ ሚኒስትር በጅግጅጋ ከተማ ወላጆቼ ታስረውብኛል አሉ

አምባ ዲጂታል፣ረቡዕ ኅዳር 1፣ 2014 ― በተያዘው ዓመት መስከረም ወር አጋማሽ ከነበሩበት የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚኒስትርነት ኃላፊነት በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን ያስታወቁት ወይዘሮ ፊልሳን ዐብዱላሂ፣ በሶማሊ ክልል መቀመጫ ጅግጅጋ ከተማ ወላጆቼ ታስረውብኛል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በትዊተር ባሰፈሩት ማስታወሻ ላይ ወላጆቼ በጅግጅጋ መታሰራቸውን ተረድቻለሁ ያሉት ወይዘሮ ፊልሳን፣ በጸጥታ አካላት ምርመራ እየተደረገባቸው ስለመሆኑም አስፍረዋል፡፡

የቀድሞዋን ሚኒስትር ወላጆች እስር በተመለከተ የሶማሌ ክልል ባለሥልጣናትም ሆኑ ከፌዴራል መንግስት በኩል እስካሁን ድረስ የተባለ ነገር የለም፡፡

ወይዘሮ ፊልሳን ዐብዱላሂ ከነበሩበት ሥልጣን መስከረም 24፣ 2014 ከተመሠረተው አዲስ መንግስት ምሥረታ ቀድመው ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን በማኅበራዊ ትስስር መድረክ ላይ ማስፈራቸው አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡

የቀድሞዋ ሚኒስትር ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዐሕመድ ባስገቡት በደብዳቤያቸው ላይ ከሥራቸው ለመልቀቅ ምክንያታቸውን በግልጽ ባያስቀምጡም፤ ‹‹ከእሴቶቼና ከታማኝነቴ ጋር ተቃራኒ የሆኑና ሥነ ምግባሬን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ነገሮች፤ እንዲሁም እነዚህን እምነቶች መካድ የራሴንና የዜጎቻችንን እምነት መጣስ በመሆኑ ነው›› ብለው ነበር፡፡

የወይዘሮ ፊልሳን ዐብዱላሂን ከፌዴራል መንግስት ሥልጣን መልቀቅ ተከትሎ በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሰው የኦጋዴን ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ውሳኔያቸውን ‹‹ድፍረት የተሞላበት›› በሚል አሞግሶታል፡፡ አያይዞም ለዓመታት ቆይቷል ያለው የሶማሌ ሕዝቦች መገፋት ያበቃል በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ምክትላቸው ደመቀ መኮንን ማረጋገጫ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም ይህን የመቀየር ፖለቲካዊ ፍላጎት እንደሌለ አሳውቋል፡፡

በሌላ በኩል ይህንኑ የኦብነግ ድጋፍ ተከትሎ ምላሽ ያወጣው ርእሰ መስተዳደሩ አቶ ሙስጠፋ መሐመድ የሚመሩት የሶማሌ ክልል አስተዳደር፣ የሶማሌ ክልል ላለፉት 50 ዓመታት ከጦርነት፣ አመጽ፣ መፈናቀል፣ አስገድዶ መድፈር እና ድርቅ ጋር ተያይዞ ቢነሳም፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ግን ሰላም እንደሰፈነበት አሳውቋል፡፡ በብሔራዊ ደረጃም ቢሆን የሶማሌ ውክልና መጨመሩን ያስታወቀው የክልሉ መንግስት፣ የክልሉ ሁኔታ ይህን ቢያመለክትም በጦርነት ለሚነግዱ ግን አሁንም የሶማሌ ሕዝብ እንደተገለለ ነው ሲል ገልጾ ነበር፡፡

ወይዘሮ ፊልሳን ዐብዱላሂ መሐመድ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ከመጋቢት 3፣ 2012 እስከ መስከረም 2014 ድረስ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img