Sunday, September 22, 2024
spot_img

የሕወሓት ኃይሎች በነፋስ መውጫ የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች መፈጸማቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሪፖርቱ ይፋ አደረገ

አምባ ዲጂታል፣ረቡዕ ኅዳር 1፣ 2014 ― ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትላናት ምሽት ባወጣው ሪፖርቱ የሕወሓት ተዋጊዎች በሴቶቹ ላይ የአስገድዶ መድፈር ጥቃቱን የፈጸሙት ነፋስ መውጫን በተቆጣጠሩበት ከነሐሴ 6 እስከ ነሐሴ 15፣ 2013 ባሉት አስር ቀናት ውስጥ ነው፡፡

የተደፈሩትን ሰዎች ቁጥር በተመለከተ የመብት ተቋሙ 16 ተጠቂዎችን ቃለ ምልልስ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፣ የአካባቢው ባለስልጣናት 71 ሴቶች ተደፍረናል በሚል ሪፖርት ማድረጋቸው ተጠቅሷል፡፡ ሪፖርቱ የፍትሕ ሚኒስቴር ይህን ቁጥር 73 እንደሚያደርሰው ጠቁሟል፡፡

በሪፖርቱ ላይ ከተጠቀሱ ሴቶች መካከል አንዳንዶቹ ተጠቂዎች የአስገድዶ መድፈር ፈጻሚዎቹ ድርጊቱን የፈጸሙባቸው በልጆቻቸው ፊት ለፊት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከተጠቂዎቹ መካከል የ28፣ የ30 እና 45 ዓመት እድሜ ያላቸው ሴቶች ታሪክ በሪፖርቱ ሠፍሯል፡፡

ተጠቂዎቹ ድርጊቱን ፈጻሚዎቹ የሕወሓት ሰዎች መሆናቸውን መለየት የቻሉት በአነጋገር ዘያቸው እና በሚሰነዝሩት ብሔርን መሠረት ባደረገ ስድብ እንዲሁም በግልጽ ሕወሓቶች መሆናቸውን ራሳቸው በመናገራቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የሕወሓት ኃይሎች በነፋስ መውጫ በቆዩባቸው ቀናት ከፈጽሟቸው አስገድዶ መድፈር፣ አዋራጅ ንግግር እና አካላዊ ጥቃቶች በተጨማሪ በተጠቂዎቹ ላይ ዘረፋና ንብረታቸው ላይ ውድመትን መፈጸማቸውን የአምነስቲ ሪፖርት አመልክቷል። ታጣቂዎቹ ከሴቶቹ ከዘረፏቸው ንብረቶች መካከል ጌጣጌጦች፣ ገንዘብ እና ተንቀሳቃሽ ስልክ ጭምር እንደሚገኝበት ተጠቅሷል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያነጋገራቸው 16 የአስገድዶ መድፈር ሰለባዎች በጥቃቱ ሳቢያ የተለያዩ አካላዊና አእምሯዊ ችግር እንደገጠማቸው የገለጹ ሲሆን፣ በአካባቢው ያሉ የህክምና ተቋማት በሕወሓት ኃይሎች በመዘረፋቸውና በመውደማቸው ሴቶቹ የህክምና ድጋፍ ለማግኘት አዳጋች እንደሆነባቸው ተቋሙ አመልክቷል፡፡  

በጉዳዩ ላይ የተናገሩት የአምነስቲ ኢንትርናሽናል ዋና ጸሐፊ አግነስ ካላማርድ ‹‹የአስገድዶ መድፈር ጥቃቱ ከደረሰባቸው የሰማናቸው ምስክርነቶች የሕወሓት ተዋጊዎችን አጸያፊ ተግባራት፤ ከጦር ወንጀሎች እና በሰብአዓዊነት ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች ጋር የሚስተካከሉ ናቸው›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ድርጊቶቹ ከሞራል ወይም ከሰብዓዊነት ያፈነገጡ›› መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት ጾታዊ ጥቃት ሰላባዎቹን እና ሌሎችም ተጎጂዎች ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ በፍጥነት እንዲያመቻች ጠይቀዋል፡፡

አያይዘውም የሕወሓት ተዋጊዎች ወሲባዊ እና ፆታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ የሰብዓዊ መብቶችን እና የዓለም አቀፍ ሕጎች ጥሰቶችን በሙሉ በማቆም በፈጻሚዎቹ ላይ ርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

ተዋጊዎቹ ድርጊቱን ፈጽመዋል በሚል የተወነጀለው ሕወሓት ይህ ዘገባ እስከተሰናዳበት ሰአት ድረስ በሪፖርቱ ላይ ያለው ነገር የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img