Sunday, September 22, 2024
spot_img

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት የአገርን ሉአላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ጥምረት እንደማይቀበል አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 29 2014 ― የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት የአገርን ሉአላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ጥምረት እንደማይቀበል በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫው አስታውቋል፡፡

በሰሜን አሜሪካ ‹‹የፌደራሊስት/ኮንፌደራሊስት ጥምረት ፈጠርን ብለው በኢትዮጵያ ፓርላማ በአሸባሪነት በተፈረጀው ህወኃት አቀናባሪነት ሲንደፋደፉ የታዩትን ግለሰቦችም ታዝበናል›› ያለው ምክር ቤቱ፣ ‹‹ይህ የኢትዮጵያን ህዝብ አለማወቅ በሌላ በኩል ግን አገራችንን ችግር ውስጥ ለመክተት የሚኬድበትን የሰይጣናዊ ጉዞ ርቀት የሚያሳይ ነው›› ብሎታል፡፡  

አያይዞም ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ ራሱ መርጦ የሚያቆመው እንጂ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ተጠፍጥፎ የሚቀመጥለትን አሻንጉሊት መንግስት በታሪክ ተቀብሎ አያውቅም›› ያለ ሲሆን፣ ዛሬም እንደማይቀበልና ምክር ቤቱም ‹‹የአገርን ሉአላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ጥምረት›› እንደማይቀበል ገልጧል፡፡  

የምክር ቤቱ መግለጫ የመጣው ከሰሞኑ ሕወሓት እና የኦሮሞ ነጻነት ጦር የተባለውን ቡድን ጨምሮ በዋሺንግተን መመስረቱን ማሳወቁን ተከትሎ ነው፡፡ በወቅቱ በዋሺንግተን በተካሄደው ሥነ ሥርዐት ላይ የጥምረቱን አላማ በተመለከተ የተናገሩት የሕወሓት ኃይሎችን በመወከል የተገኙት አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ፣ አላማቸው የኢትዮጵያ መንግሥትን በኃይል አልያም በድርድር በማስወገድ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት እቅድ እንዳላቸው አስታውቀው ነበር፡፡

ጥምረቱን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን የተናገሩት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ፣ ጥምረቱ ይህ ነው የሚባል የፖለቲካ መሰረት የሌለው ደካማ ስብስብ ነው ሲል አጣጥለውታል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት በሬው እለት ባወጣው መግለጫም ጥምረቱን ‹‹ለሕጋዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቀናኢ የሆኑ ሁሉም ተቋማትና አገሮች ይህን ጣልቃ ገብነት ማውገዝ ይኖርባቸዋል›› ብሏል፡፡

በሌላ በኩል በአስፈፃሚ እና የቋሚ ኮሚቴ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ ማድረጉን ያመለከተው ምክር ቤቱ፣ በአምስት ጉዳዮች ላይ አቋሙን አሳውቋል፡፡

በዚህም በዚህ ፈታኝ ወቅት ሁሉም ዜጋ በተለይ የቀድሞ ሰራዊት አባላትና የውትድርና ስልጠና ያላቸው ሁሉ ነቅቶና ተደራጅቶ አገሩ የምትጠይቀውን ሁሉ መስዋዕትነት በመክፈል ኢትዮጵያን ከውጭም ሆነ ከውስጥ ችግር ፈጣሪዎች እንዲጠብቅ፣ በዚህ ጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም መንግሥት ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ ዜጎች በሙሉ ኃይል እንዲረባረቡ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ንፁሐን ዜጎች (በተለይ የትግራይ ተወላጆች) ላይ እንግልት እንዳይደርስ በአፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ፣ መንግሥት ከአገራዊ መግባባት መድረኩ ገለልተኛ ሆኖ ሂደቱ የሚጀመርበትን እና የሚፋጠንበትን ሁኔታ በማመቻቸት ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንዲሁም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የ21ኛውን ክ/ዘመን በሚመጥን ደረጃ የሃሳብ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት እንዲዘጋጁ በማለት ጥሪውን አቅርቧል፡፡  

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img