አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 29፣ 2014 ― የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ማኅበር በተለይ በቅርብ ጊዜያት ኢትዮጵያን በተመለከተ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርን ያልተከተሉ ዘገባዎች መሠራጨታቸው አሳሳቢ መሆኑን ገልጧል፡፡
ማኅበሩ ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የሚዘገቡት አንዳንድ ዘገባዎች ትክክለኛ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርን ያልተከተሉ በዋናነትም ትክክለኛ መረጃን የማቅረብ መርሆን ያልያዙ በመሆናቸውም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳሳተ መረጃ ሲያሰራጩ መስተዋሉን ገልጧል፡፡
ማህበሩ ለዚሁ አስረጂ በማለት ‹‹ትክክለኛነትና ሚዛናዊነቱን ለማጣራት›› ጥረት እንዳደረገበት የገለጸውን አዲስ አበባንና ዙሪያዋን በተመለከተ የተሰራጩ ዘገባዎችን ጠቅሷል፡፡ ማኅበሩ እነዚህን ዘገባዎች ተከትሎ ‹‹ለዘገባ ከተንቀሳቀሱ እና በየአካባቢው ከሚኖሩ አባሎቻችን ብሎም ከነዋሪዎች ባገኘነው መረጃ መሰረት ይህ መግለጫ እስከተፃፈበት ጊዜ ድረስ አዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙት አካባቢዎች ሁሉ በተለመደው እንቅስቃሴያቸው ላይ ይገኛሉ›› ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች በማሳያነት የጠቀሰውን አዲስ አበባ እና ዙሪያዋን የሚመለከት ዘገባ ካቀረቡት መካከል የአሜሪካው የኔትወርክ ቴሌቪዥን ሲኤንኤን የሚጠቀስ ሲሆን፣ ጣቢያው በዚህ ዘገባው የታጠቁ አማጺያን አዲስ አበባ ዙሪያ እንደሚገኙ ዘገባ ሠርቷል፡፡ ይህንኑ ተከትሎም ጣቢያው ሐሰተኛ ዘገባ አሠራጭቷል በሚል በተለይ በኢትዮጵያውያን ትዊተር ተጠቃሚዎች በከፍተኛ ሁኔታ ውግዘት አስተናግዷል፡፡
ይህንኑ ዘገባ አስረጂ ያደረገው ማኅበሩ፣ ‹‹የተዛቡ፣ ትክክለኛ የጋዜጠኝነት መርህን ያልተከተሉ፣ የአገር ሉዓላዊነትና የህዝቦችን አንድነት አደጋ ውስጥ የሚጥሉ ብሎም ፖለቲካዊ ውግንና›› አላቸው ያላቸውን መሰል ዘገባዎች ያሠራጩ መገናኛ ብዙኃንን ኮንኗል፡፡
አያይዞም ‹‹በእንደዚህ ያሉ ሙያዊ መርሆን ባልተከተሉ ዘገባዎች›› እየተሳተፉ ያሉ ጋዜጠኞችን ጋዜጠኝነታቸውን በሙያዊ አስተምህሮው መሰረት እንዲፈፅሙ ጠይቋል፡፡
በተጨማሪም ማህበሩ ‹‹መቀመጫቸውን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለም ያደረጉና ስለኢትዮጵያ የሚዘግቡ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ባለሙያዎች›› ከእንደዚህ አይነት አዘጋገብ እንዲወጡ አጥብቆ ያሳሰበ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግስትና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም የየትኛውም መገናኛ ብዙኃን ዘጋቢዎች ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙ እና በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው እውነተኛ መረጃ ለህዝብ ማቅረብ እንዲችሉ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንደሚገባቸውም አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩል የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃንም ፈጣን፣ ወቅታዊ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃዎችን እንዲያቀርቡ መክሯል፡፡