Sunday, November 24, 2024
spot_img

በተመድ እና ኢሰመኮ ጥምረት የተካሄደው የሰብዐዊ መብት ምርመራ ገለልተኛ እና ተጠያቂነትን ሊያሰፍን የሚችል ነው ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ጥቅምት 28፣ 2014 ― በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጥምረት የተካሄደው የሰብዐዊ መብት ምርመራ ገለልተኛ እና ተጠያቂነትን ሊያሰፍን የሚችል መሆኑን የገለጹት አሜሪካና እንግሊዝን ጨምሮ 16 ሀገራት ናቸው።

አሜሪካን እና እንግሊዝ ያሉበት ስብስብ በኢትዮጵያ የተካሄደውን ጥምር ምርመራ ሪፖርት እንደሚቀበሉትም አሳውቀዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በትግራይ ግጭት ዙሪያ ያደረጉትን የጋራ ሪፖርት ይፋ ያደረጉት ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ነበር።

በሪፖርቱ በግጭቱ ተሳታፊ አካላት መጠኑ ቢለያይም የሰብአዊ መብት እና ዓለም አቀፍ የስደተኞች መብት ጥሰቶችን ጨምሮ እስከ ጦር ወንጀል ሊደርሱ የሚችሉ ጥሰቶችን መፈፀማቸው ተጠቅሷል።

ለዚሁ ሪፖርት እውቅና የሰጡት አገራት አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂየም፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ አይስላንድ፣ አየርላንድ፣ ሉግዘንበርግ፣ኔዘርላንድ፣ ኒውዝላንድ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን እና እንግሊዝ ናቸው።

ሀገራቱ በጋራ መግለጫቸው የጋራ ሪፖርቱ ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነትን ከማስፈን ባለፈ ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ እየተበራከቱ በመጡ ጥቃቶች ዙሪያ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ በር የሚከፍት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህ ሪፖርት መሰረት በጥቃቱ ሁሉም አካላት ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የህወሓት ታጣቂዎች፣የኤርትራ ሰራዊት እና በህወሃት የተደራጁት ሳምረ የተሰኘው የወጣቶች ቡድን መሳተፋቸው በሪፖርቱ በመረጋገጡ ሁሉም ተሳታፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ሀገራቱ አሳስበዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ ላይ የተሳተፉ ሁሉም አካላት በሪፖርቱ ግኝቶች መሰረት ወደ መፍትሄ እንዲመጡም አክለዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ እነዚህ አገራት የኢትዮጵያ መንግስት በጦርነቱ ለተጎዱ አካላት እያደረገ ያለው ድጋፍ፣ ወንጀል ፈፅመዋል በሚል በተጠረጠሩ አካላት ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ምርመራ መጀመሩ እና እያደረጋቸው ላለው ሌሎች ጥረቶች እውቅና እንደሚሰጡ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።

መንግስት የጀመረውን ጥረት እንዲቀጥልበት የጠየቁት እነዚህ ሀገራት፤ በተለይም ለተጎጂዎች ተጨማሪ የሰብዓዊ መብት ድጋፎች እንዲደርሱ፣ በወንጀል ፈጻሚዎች ላይ ተጨማሪ ምርመራዎች እንዲካሄዱ እና ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም ብሄራዊ ውይይት እንዲያካሂድም አሳስበዋል።

ሀገራቱ ከዚህ ባለፈ ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እና መረጋጋቷ እንድትመለስ ድጋፍ እንደሚያደርጉና የግዛት አንድነቷን እንደሚያከብሩ በመግለጫቸው አሳውቀዋል።

ሪፖርቱን በተመለከተ መንግስት ክፍተቶች እንዳሉበት በመጥቀስ ሲቀበለው፣ ሕወሓት ይፋ ሳይደረግ ቀድሞ ውድቅ አድርጎታል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img