አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 25፣ 2014 ― ከትላንት በስትያ ማክሰኞ ጥቅምት 23፣ 2014 የባይደን አስተዳደር ባስተላለፈው ውሳኔ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የአጎዋ ተጠቃሚነት እድል ከመጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ጀምሮ እንደምታግድ ማሳወቋ ይታወቃል፡፡
በጉዳዩ ላይ መልስ የሰጠው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በውሳኔው ማዘኑን በመግለጽ አሜሪካ ለእጋደው ምክንያት ነው ያለችውን በሰብዓዊ መብቶች ያላትን ስጋት ቢረዳም፣ ሁኔታው ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት እድል የማገድ ውሳኔ ላይ እንደማያደርስ በማስገንዘብ ተችቶታል፡፡
ውሳኔውንም የተሳሳተና የአሜሪካ መንግሥት ለዜጎች ደህንንት ያለውን ቁርጠኝነት ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያን ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት እድሉ ከ200 ሺሕ በላይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ቤተሰቦች ላይ ተፅእኖ እንደሚኖረው ጠቅሷል፡፡ ይኸው ተጽእኖ በተለይም ከግጭቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሴቶች ላይ ጉዳቱ ይበረታል ያለ ሲሆን፣ በአቅርቦት ሰንሰለቱ የሚሳተፉትን የአንድ ሚሊዮን ነዋሪዎችን ሕይወት በእጅጉ እንደሚጎዳም ነው የገለጸው፡፡
መንግሥት አያይዞም ከዚህ ይልቅ ኢትዮጵያውያን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና በተለይም ከአሜሪካ በአሁኑ ወቅት የሚጠብቁት ነገር ለተጎጂዎች በጣም አስፈላጊ የሆነውን የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እንደሆነም ጠቅሷል።
አያይዞም የንፁኃን ዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል የሚደረጉ ማስፈራራቶች ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ አይሰጥም ያለው መንግስት፣ ከዚህ ጀርባ ያሉትም የኢትዮጵያ ጠላቶች ናቸው ብሎ እንደሚያምንም በመግለጫው አመልክቷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለአሜሪካ ኮንግረስ በጻፉት ደብዳቤ ኢትዮጵያ ‹‹በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የታወቁ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን›› ፈጽማለች ብለዋል፡፡ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ተጨማሪ ማሊ እና ጊኒን በቅርብ ወራት ውስጥ በተከሰቱት መፈንቅለ መንግሥት ምክንያቶች ማገዷን አሳውቃለች፡፡