Saturday, November 23, 2024
spot_img

የመንግሥታቱ ድርጅት ከኢሰመኮ ጋር ያደረጉት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሪፖርት ይፋ ተደረገ


አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 24፣ 2014 ― በዛሬው እለት አንድ ዓመት በደፈነው በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አጎራባች አፋር እና አማራ ክልሎች ከተስፋፋው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ሲካሄድ የነበረው የምርመራ ውጤት ይፋ ተደርጓል፡፡

በዛሬው እለት በኢሰመኮ ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ሚሼል ባችሌት ይፋ የተደረገው ሪፖርት፣ የትግራይ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻዎች ጥቅምት 24፣ 2013 ፈጽመውታል ካለው የሰሜን እዝ ሠራዊት ጥቃት እስከ ሰኔ 21፣ 2013 ማለትም የፌዴራል መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ትግራይን ለቆ እስከወጣበት ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ነው።

በዚህ ባለ 22 ገጾች ሪፖርት የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ኃይል፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ፋኖ በአንድ ወገን እንዲሁም የትግራይ ልዩ ኃይል፣ የትግራይ ሚሊሻ እና ሌሎች ቡድኖች በሌላ ወገን ሆነው በጦርነቱ መሳተፋቸውን ተጠቅሷል፡፡

ሁለቱ አካላት በጋራ ባደረጉት ምርመራ፣ በትግራይ ግጭት የተሳተፉ ሁሉም አካላት የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ያስታወቁ ሲሆን፣ በግጭቱ ተሳታፊ አካላት በተለያየ መጠን ተፈጽመዋል ከተባሉት ጥሰቶች ውስጥ የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ይገኙበታል።

የጋራ የምርመራ ቡድኑ በምርመራ ወቅት ያገኛቸውን ግኝቶች ከፋፍሎ አቅርቧል፡፡ በዚህም ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎችን እንዲሁም ርሸናዎች፣ ከሕግ ውጭ የተደረጉ ስቅይቶች፣ የዘፈቀደ እስራቶችን፣ በስደተኞች ላይ የተፈጸሙ ግፎች እንዲሁም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሱ የኃይል ማፈናቀሎች ተዘርዝረዋል፡፡

ሪፖርቱ በንጹሐን ላይ የተፈጸሙ ግኝቶችን ሲዘረዝር፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ኃይል እና የትግራይ ልዩ ኃይል ባደረሱት ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን አመልክቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጤና ማእከላት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የእምነት ስፍራዎች እና መኖሪያ ቤቶች ወድመዋል ብሏል፡፡

በጦርነቱ ተፋላሚ አካላት በንጹሐን ላይ ጥቃት ደርሷል ተብለው ከተጠቀሱ ከተሞች መካከል መቐለ፣ ሑመራ፣ ውቅሮ እና ጎንደር ይገኙበታል፡፡ ሪፖርቱ በመቐለ ለደረሰው የንጹሐን ጥቃት የአገር መከላከያ ሠራዊትን ተጠያቂ ሲያደርግ፣ በሑመራ ለደረሰው የኤርትራ መከላከያ ኃይል እና የትግራይ ልዩ ኃይልን ተጠያቂ ናቸው ብሏል፡፡ በውቅሮ የደረሰው የንጹሐን ሞት ደግሞ በአገር መከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ ልዩ ኃይል መካከል በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ የተፈጸመ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

የምርመራ ቡድኑ በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረቱ ግድያዎች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ደርሶኛል ያለ ሲሆን፣ ይህ በተለይም ወጣት ወንዶች ላይ ያነጣጠረ ነው ብሏል፡፡ ለዚህ አስረጂ በማለት ከቀረቡት ክስተቶች መካካል በማይካድራ ከተማ ‹‹ሳምረ›› ተብሎ በሚጠራ ቡድን የተፈጸመ ጥቃት ይገኝበታል። በዚህ ጥቃት ምንም እንኳን ቁጥሩን ርግጠኛ ለመሆን ባይቻልም ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለው በጅምላ መቃብሮች መቀበራቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል።

የመከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ልዩ ኃይል የሁመራ ከተማን በተቆጣጠሩባቸው ቀጣይ ቀናት በተመሳሳይ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የማይካድራ ከተማ ነዋሪዎች ላይ የበቀል ግድያዎች መፈጸማቸውን እና የፋኖ ሚሊሺያዎችም በግድያው መሳተፋቸውን መርማሪ ቡድኑ መረዳቱን ገልጿል።

በተጨማሪም በአክሱም ከተማ የኤርትራ ሠራዊት አባላት ከ100 በላይ ሲቪሎችን መግደላቸውን እንዲሁም በወቅቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ግድያዎቹ ሲፈጸሙ ጣልቃ ሳይገቡ መቅረታቸውን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚን በጋራ ባወጡት ሪፖርት ማሳረጊያ ላይ ምክረ ሐሳቦችን አቅርበዋል፡፡ በዚህ ምክረ ሐሳብ በሁሉም ወገኖች በኩል ለተፈጸሙ በደሎች ተጠያቂነት እንዲኖር የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አጥፊዎችን ለፍርድ ካላቀረቡ ጉዳዩ ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲሄድ እንደ አንድ አማራጭ አስቀምጠዋል፡፡

በፍትህ አሰጣጥ አማራጮች ትግበራ ወቅት እነዚህን ሰብአዊ መብት ጥሰቶች በዋናነት የማረም ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ የጠቀሱ ሲሆን፣ በአጥፊዎች ላይ የወንጀል ክስ በመመስረት፣ የዲሲፕሊን እርምጃዎችን በመውሰድ እንዲሁም አስተዳደራዊ ምርመራዎችን በማካሄድ ስልታዊ ጥቃቶችን እንዲለይ በሪፖርቱ ምክረ ሃሳብ ላይ ተቀምጧል።

በዛሬው እለት የወጣው ሪፖርት ይፋ ከመደረጉ ቀድሞ የሕወሃት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ፣ በትዊተር ባሰራጩት ምላሽ፣ የምርመራውን ሂደትም ሆነ ውጤት እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል። ኢሰመኮ በምርመራው መሳተፉ ተአማኒ ምርመራ እንዳይሆን አድርጎታል፣ ምርመራውም ቢሆን ሁሉንም ጥፋት የተፈጸመባቸውን የትግራይ አካባቢዎች አላካተተም ያሉት ጌታቸው፣ ድርጅታቸው ሕወሓት በምርመራው ሂደት አልተሳተፈም በሚልም ሪፖርቱን አጣጥለውታል።

በሌላ በኩል ሪፖርቱን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በለቀቁት ማስታወሻ፣ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የጋራ መርማሪ ቡድኑ በዚህ ውስብስብ ጉዳይ ላይ ሙያዊ ደረጃውን የጠበቀ እና ጥልቀት ያለው የምርመራ ሪፖርት በማዘጋጀቱ በማድረጉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡


ሆኖም የሪፖርቱን አንዳንድ ድምዳሜዎችን በተመለከተ መንግስታቸው ጥርጣሬ እንዳለው አስፍረዋል፡፡ ከነዚህ መካከል የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደፈጸመና ሆን ብሎ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለትግራይ ክልል እንዳይደርስ በማድረግ ርሃብን እንደ መሳሪያ ተጠቅሟል መባሉን ውሸት ከመሆኑም በላይ ጠላት ያሉት አካል ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማታለል ደጋግሞ ሲለው የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡


የፌዴራል መንግሥት ውስንነቶች አሉበት ያለውን ይህ ሪፖርት ሳያካትታቸው ቀርተዋል ያላቸውን ነገሮችንም መጥቀሱ ተነግሯል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሕወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች ሕጻናትን፣ ሴቶችን እና አረጋዊያንን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የፈጸማቸውን ግድያዎች፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን እና ዕድሜያቸው ለተዋጊነት ያልደረሱ ታዳጊዎችን ለጦርነት ማሰለፉን የመሳሰሉ ወንጀሎችን እንደሆነ ጠቅሷል።

ሆኖም ምርመራ ሪፖርቱ በሚሸፍነው ጊዜ ውስጥ ሕወሃት ትግራይ ውስጥ የፈጸማቸውን ከባድ ወንጀሎች ሪፖርቱ ማጋለጡ እንዳስደሰተው መንግሥት ሳይጠቅስ አላለፈም።

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ኢሰመኮ ይፋ ያደረጉት ምርመራ ከግንቦት 8 እስከ ነሐሴ 14፣ 2013 ድረስ የተደረገ ሲሆን፣ መቐለ፣ ውቅሮ፣ ሳምረ፣ አላማጣ፣ ቦራ፣ ማይጨው፣ ዳንሻ፣ ማይካድራ፣ ሑመራ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር እና አዲስ አበባ ከተሞችን አካቷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img