አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ጥቅምት 20፣ 2014 ― የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ሕወሃት ተዋጊዎቹን ከአማራ እና አፋር ክልል እንዲያስወጣ እንዲሁም ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች የሚያደርገውን ግስጋሴ እንዲገታ አሳስቧል።
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አክሎም የሕወሃት ተዋጊዎች በከተሞች ላይ ከባድ መሳሪያዎችን ከመተኮስ እንዲቆጠቡ ያሳሰበ ሲሆን፣ ሁሉም ወገኖች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
በሌላ በኩል የትግራይ ክልል ተረጂዎችን በተመለከተም ያነሳው መግለጫው፣ ለትግራይ ክልል ተረጅዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳይቀርብ መንግሥት እገዳ እንደጣለ ቀጥሏል ሲል ወቀሳ ሰንዝሯል።
የሕወሓት ኃይሎች ደሴ ከተማን ተቆጣጥረናል ማለታቸው ተዘገበ
- የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ ደሴ በመከላከያ ቁጥጥር ስር መሆኗን በመግለጽ “አንዳንድ የውጪ መገናኛ ብዙሃን የሽብር ቡድኑን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ እያስተጋቡ ይገኛሉ” ብሏል
የአሜሪካ መግለጫ የመጣው የሕወሓት ኃይሎች ደሴ ከተማን መቆጠጠራቸውን መናገራቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።
የሕወሃት ኃይሎች ከተሞቹን ተቆጣጥረናል ማለታቸው በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ቢዘገብም፣ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ አሁንም ደሴና አካባቢዋ “በፀጥታ ሃይላችን ስር ነው” ብሏል።
አገልግሎቱ “ደሴን ለመያዝ አሰፍስፎ” መጥቷል ያለው የሕወሃት ኃይል “በመመከት አኩሪ ገድል” እየተፈፀመ ይገኛል ሲል አክሏል።
አያይዞም “አንዳንድ የውጪ መገናኛ ብዙሃን የሽብር ቡድኑን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ እያስተጋቡ ይገኛሉ” ያለው የኮሚኒኬሽን አገልግሎቱ፣ “በወሬ የሚያዝ ከተማ የለም ሊኖርም አይችልም” በማለት፣ በተለይ ያልተጣራ መረጃን በመያዝ “ህዝብን ለማሸበር እየተንቀሳቀሱ የሚገኙና የሽብር ቡድኑ መጠቀሚያ የሆኑ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ” ሲል አሳስቧል።
ሬውተርስ የሕወሃት ቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ ካልታወቀ ቦታ በሳተላይት ስልክ ደሴን ተቆጣጥረን ወደ ኮምቦልቻ እያቀናን ነው ብለውኛል ሲል አስነብቧል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት አገርሽቶ በከፍተኛ ሁኔታ የቀጠለው የፌዴራል መንግስት እና የሕወሃት ኃይሎች ጦርነት በሚቀጥለው ሳምንት አንድ ዓመት ይደፍናል።
ባለፉት ቀናት የፌዴራል መንግሥት ወደ መቐለ ከተማ የአየር ላይ ጥቃቶችን ማድረጉን በተደጋጋሚ አሳውቋል። የሕወሓት ኃይሎቾ በበኩላቸው ወደ ደሴ ከተማ የመድፍ አሩር መተኮሳቸው ሲነገር ነበር። በሁለቱም በኩል በተሰነዘሩ ጥቃቶች ንጹሐን ሕይወታችው መነጠቁን መረጃዎች ጠቁመዋል።