Wednesday, November 27, 2024
spot_img

ሕወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ከ400 በላይ ሰዎችን መግደሉን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ

በፍትሕ ሚኒስቴር የዐቃቤ ሕግ ዘርፍ እና የፌደራል ፖሊስ የምርመራ ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች ያካሄዱትን የመጀመሪያ ደረጃ የወንጀል ምርመራ ውጤት ይፋ አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሪፖርቱ የሕወሓት ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች ከ482 በላይ ንጹሃን ሰዎችን ገድለዋል ብሏል፡፡

የምርመራ ቡድኑ ከግድያው በተጨማሪ በሁለቱ ክልሎች 165 የአካል ጉዳቶች እንዲሁም 109 የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች በሕወሓት ኃይሎች ተፈጸመዋል ብሏል።

የሕወሓት ኃይሎች ወደ አጎራባች አማራ እና አፋር ክልሎች ገፍቶ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ሰዎን ገድሏል የተባለው የፌዴራል መንግስት በሰኔ ወር 2013 መገባደጃ ትግራይን ለቆ መውቱን ካሳወቀ በኋላ ነው፡፡

አንድ ዓመት ሊደፍን ቀናት የቀሩት በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው እና ወደ አጎራባች ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት በርካታ ሺዎችን መቅጠፉ ይነገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ለሰብዓዊ እርዳታ ዳርጓቸዋል፡፡

በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑት አካላት በሙሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል በሚል በተደጋጋሚ ክስ ሲቀርብባቸው ቆይቷል።

አሁን የተካሄደው ምርመራ የተካሄደው በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ በፌደራል ፖሊስ እንዲሁም ከክልል አካላት ጋር በትብብር በተዋቀረ የዐቃቤ ሕግ እና የፖሊስ የምርመራ ቡድን ነው።

በደቡብ ጎንደር ዞን የተሰማራው የምርመራ ቡድን ከ790 በላይ ምስክሮችን የምስክርነት ቃል፣ በሰሜን ጎንደር ዞን የተሰማራው የምርመራ ቡድን ደግሞ 285 የምስክሮች ቃል እንዲሁም በአፋር ክልል የተሰማራው ቡድን 148 ምስክሮች ቃል መቀበሉን አመልክቷል። ከምስክርነት ቃል በተጨማሪ ተፈጽመዋል የተባሉት የወንጀል ድርጊቶችን ሊያስረዱ የሚችሉ የሰነድ ማስረጃዎች አሰባስቤያለሁ ብሏል።

ፍትሕ ሚኒስቴር ካወጣው ሪፖርት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጋር በመሆን በትግራይ እና በአማራ ክልል በጋራ ያደረጉት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የምርመራ ሪፖርት በመጪው ሳምንት ረቡዕ ይፋ እንደሚደረግ ተጠብቋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንዔል በቀለ እና የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ሚሸል ባቸሌት በሪፖርቱ ግኝቶች፣ ድምዳሜዎች እና ምክረ ሃሳቦች ላይ በአዲስ አበባ እና በጀኔቫ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ነው የተገለጸው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img