Sunday, September 22, 2024
spot_img

በደሴ በትላንትናው እለት በተተኮሰ የከባድ መሣሪያ የሰው ሕይወት መቀጠፉ ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ጥቅምት 20 2014 ― በደሴ ዙሪያ በስፋት እየተካሄደ መሆኑ በሚነገረው የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓት ኃይሎች ውጊያ ሐሙስ ዕለት ወደ ከተማዋ በተተኮሱ አምስት የመድፍ አረሮች አንድ ሰው የሞተባት ደሴ ከተማ፣ ትላንት ዐርብም በከባድ መሳሪያ ጥቃት አንድ ተጨማሪ ነዋሪዋ መሞቱን ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው አቶ ሰዒድ ዩሱፍ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ወደ ከተማዋ ከሕወሓት ኃይሎች በሚተኮስ የከባድ መሳሪያ እስከ ትላንት ድረስ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፣ አስር ያህል ሰዎች ደግሞ የተለያዩ ጉዳት አጋጥሟቸው ሕክምና በመከታተል ላይ ይገኛሉ።

ትላንት ዐርብ ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ተተኮሰ ባሉት በዚህ ከባድ መሣሪያ ከአንድ ሰው ሞት ውጪ ሌላ ጉዳት ስለመድረሱ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።

በፌደራል መንግስት ኃይሎችና በሕወሓት ኃይሎች መካከል ባለፉት ቀናት በዙሪያዋ ውጊያ ሲካሄድ በቆየችው ደሴ፣ ትላንት ስምንት ሰዓት አካባቢ ‹‹ወደ ከተማዋ የሕወሓት ኃይሎች ገብተዋል የሚል ወሬ ተሰራጭቶ›› እንደነበር የተናገሩት ምክትል ከንቲባው፣ በከተማው ነዋሪ ዘንድም መደናገጥ ተፈጥሮ እንደነበር ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ቢቢሲ አናገርኳቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ዐርብ ከሰዓት በኋላ በከተማዋ አንድ ክፍል በሚገኘው የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ከባድ የተኩስ ልውውጥ መስማታቸውን ገልጸው፣ ይህም በነዋሪው ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮ ነበር ብለዋል።

ነዋሪዎቹ ምን እንደተከሰተ እንዳላወቁና ነገር ግን የሕወሓት ተዋጊዎች ወደ አካባቢው ገብተው ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ያደረጉት የተኩስ ልውውጥ እንደሆነና ወደ ከተማው ገብተዋል ተብሎ እንደነበር ገልጸዋል።

ምክትል ከንቲባውም በከተማዋ የሚገኙ የመከላከያ ኃይሎችን እንቅስቃሴ ያዩ እና ‹‹በሐሰተኛ ወሬ የተደናገጡ›› ያሏቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ሌላ አካባቢ መሸሽ ጀምረው እንደነበር፣ ነገር ግን ኋላ ላይ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ መረጋጋታቸውን ተናግረዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ስለክስተቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው በጣት የሚቆጠሩ ያላቸው የሕወሓት ታጣቂዎች የተኩስ እሩምታ በመክፈት የአካባቢውን ሕዝብ ለማደናገር ሞክረዋል ብሏል።

የትግራይ ኮሚኒኬሽን ቢሮ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ትላንት አመሻሹን ባሰፈረው መረጃ ‹‹የትግራይ ሰራዊት›› ሲል የጠራው ቡድን ደሴ ከተማን መቆጣጠር ጀምሯል ብሎ ነበር፡፡

በተቃራኒው በዛሬ እለት መግለጫ የሰጡት የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊው ዶክተር ለገሠ ቱሉ፣ የሕወሓት ኃይሎች ባለፋት ጥቂት ቀናት ያላቸውን ሀይል አሰባስበው በወረባቦ፣ በተሁለደሬ እና በጭፍራ ጥቃት ከፍተዋል ያሉ ሲሆን፣ የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ ‹‹የሕወሃት አባላት ሙትና ቁስለኛ ሆነዋል›› ብለዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img