Monday, October 7, 2024
spot_img

የኤፍ ኤም ራድዮ ጣቢያዎች የውጭ አገራት ሚዲያ ፕሮግራሞችን ተቀብለው እንዳያስተላልፉ ተከለከለ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ጥቅምት 20 2014 ― የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የኤፍ ኤም ራድዮ ጣቢያዎች የውጭ አገራት ሚዲያ ፕሮግራሞችን ተቀብለው እንዳያስተላልፉ ከልክሏል፡፡

ባለስልጣኑ ፕሮግራሞቹን የሚያስተላልፉ የኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ ክልከላውን የጣለው በትላንትናው እለት ጥቅምት 19፣ 2014 ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ የተናገሩት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውጭ ሚዲያ ፕሮግራሞችን በቀጥታ (ሊንክ) በማድረግ የሚያስተላልፉ ኤፍ ኤሞች እንደተመለከቱ ገልጸው፣ ባለፈቃዶቹ ውስን የሕዝብ ሀብት ነው ያሉትን የራድዮ ሞገድ ‹‹ከታሰበለት አላማ ውጪ›› ተጠቅመዋል ብለዋል፡፡ በዚህም ከውጭ ሚዲያዎች በሊንክ ማስተላለፋቸውን እንዲያቆሙ እንደተወሰነ ነው ያመለከቱት፡፡

አዲስ አበባ ከተማን መቀመጫቸው ካደረጉት የኤፍ ኤም ራድዮ ጣቢያ መካከል ኢትዮ ኤፍ ኤም እና አሐዱ ኤፍ ኤም የተሠኙ ጣቢያዎች በውጪ አገራት የሚዘጋጁትን የአሜሪካ ድምጽ፣ ዶይቸ ቬለ እና ቢቢሲ አማርኛን በተለያዩ ጊዜያት ሲያሰራጩ ቆይተዋል፡፡ በተመሳሳይ ዋዜማ ራድዮም በተመሳሳይ በቀጥታ ሥርጭት ባይሆንም በኢትዮ ኤፍ ኤም ሲተላለፍ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ባለሥልጣኑ ክልከላውን ባብራራበት መግለጫ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች የውጭ ሚዲያ ፕሮግራሞችን በቀጥታ ተቀብለው ሲያስተላልፉ፤ ጣቢያዎቹ ቁጥጥራቸው የላላና የመጣላቸውን እንዳለ ከማስተላለፋቸው ባለፈ፣ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበና ብሔራዊ ጥቅምን የሚጎዳ እንደሆነ ገልጧል፡፡

አያይዞም ሊንክ ተደርገው የሚተላለፉ ፕሮግራሞች ላይ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ለራድዮ ጣቢያዎቹ ተገቢውን ግብረ መልስ ለመስጠትና በሕግ የተጣለበትን ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነት ለመወጣት ባለመቻሉ ክልከላውን ማስተላለፉን ነው ያመለከተው፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ክልከላውን ባብራራበት መግለጫ የሬድዮ ባለፈቃዶች በማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዲሁም ‹‹የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ ይዘቶችን›› በማዘጋጀት ለኅብረተሰቡ መረጃ ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡

ውሳኔውን ያሳለፈው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቀድሞ ከነበረው ከኅትመትና ከብሮድካስት ሚዲያ በተጨማሪ፣ በበይነ መረብ አማካኝነት የሚሰራጭ የኦንላይን ሚዲያንና እና የማህበራዊ ሚዲያን እንደ መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የሚቆጣጠር መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ባለስልጣኑ በቅርብ ጊዜያት በበይነ መረብ የሚተላለፍ ይዘት የሚያዘጋጁ ሚዲያዎች እንዲመዘገቡ ማድረጉም ይታወሳል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img