Saturday, September 21, 2024
spot_img

ኢዜማ ራስን በራስ ከማስተዳደር እና ከመዋቅር ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶችን ለማስቀረት ሕገ መንግስቱ መሻሻል አለበት አለ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥቅምት 19፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ተሻሽሎ ዘውግን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት እና አደረጃጀት እስካልተቀየረ ድረስ ግጭቶችን ማስቀረት አስቸጋሪ ነው ብሏል፡፡

ፓርቲው ይህን ያለው በዛሬው እለት ባወጣውና በአገሪቱ በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ትኩረት እንዲሰጥ በጠየቀበት መግለጫው ነው፡፡

ወቅቱ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በበርካታ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተከባ ያለችበት ነው ያለው ኢዜማ፣ በተለይም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል እየተደረገ ያለው ጦርነት ለሀገራችን ብዙ ስጋትን የደቀነ እና አሁንም የሁሉንም ልዩ ትኩረት የሚሻ እና ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን አስታውሷል፡፡

ፓርቲው በተመሳሳይ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክንያቶች እየተከሰቱ ያሉ አደጋዎች የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት እየቀጠፉ፣ ዜጎችን ከመኖሪያቸው እያፈናቀሉ እና እንሰሳትን፣ ሰብልን እንዲሁም ንብረትን እያጠፉ መሆኑንም ተገንዝቤያለሁ ነው ያለው፡፡

በማሳያነትም በኦሮሚያ ቦረና ዞን፣ በደቡብ ኦሞ ዳሳነች ወረዳ፣ በአማሮ ልዩ ወረዳ፣ በደራሼ ልዩ ወረዳ እና ኮንሶ ዞን ሠገን ዙሪያ ወረዳ እና ባስኬቶ ልዩ ወረዳ ተፈጥረዋል ያላቸውን ክስተቶች ዘርዝሯል፡፡

ፓርቲው በዘረዘራቸው አካባቢዎች ዜጎች ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ጨምሮ ሰላም እና ደህንነታቸው እየታወከ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ኢዜማ በተለይ በተለይ ራስን በራስ ከማስተዳደር እና ከመዋቅር ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት የፈጠራቸው ናቸው ብሏቸዋል፡፡

በመሆኑም አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ተሻሽሎ ዘውግን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት እና አደረጃጀት እስካልቀየረ ድረስ መሰል ግጭቶች ማስቀረት በእጅጉ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ማሻሻያ እስኪደረግበት ወይም ለዜጎች ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ ሥርዓት በሀገሪቱ እስኪተገበር ድረስ ዜጎችን የመጠበቅ እና አካባቢዎችን የማረጋጋት ስራ በመንግሥት፣ በባለድርሻ አካላት እና በማኅበረሰቡ ርብርብ ሊሰራ የሚገባ መሆኑን በጥብቅ አሳስቧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img