Sunday, September 22, 2024
spot_img

ዩኤስኤድ የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት እርዳታ ሰጪ ተቋማት ተረጂዎች ጋር እንዲደርሱ የጣሉትን ገደብ እንዲያነሱ ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 18፣ 2014 ― የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤድ) የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት እርዳታ ሰጪ ተቋማት ተረጂዎች ጋር እንዲደርሱ ገደብ እንዲያነሱ የጠየቀው በአስተዳዳሪው ሰማንታ ፓወር ረዳት በሆኑት ሳራ ቻርልስ በኩል ነው፡፡

ከሰሞኑ ኢትዮጵያ የነበሩት ሳራ ቻርልስ፣ በአራት ቀናት ቆይታቸው ከሰብአዊ እርዳታ ተቋማት እንዲሁም ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እንደተወያዩ ዩኤስኤድ በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

እንደ መግለጫው ከሆነ ሳራ በአዲስ አበባ እና በባሕር ዳር የመንግሥት ባለሥልጣናትን ያነጋገሩ ሲሆን፤ የእርዳታ ሰጪዎች ሕይወት አድን ሥራቸውን ማከናወን እንዲችሉ መንግሥት በትግራይ ክልል የስልክ እና ኢንተርኔት እንዲሁም የባንክ አገልግሎትን እንዲመልስ ጠይቀዋል።

ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ያለ ምንም ገደብ እንዲያልፉ እና የሰብአዊ እርዳታ በረራ ቁጥር እንዲጨምርም የጠየቁት ኃላፊዋ፣ የነዳጅ፣ የገንዘብ፣ የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶች እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱንም ጠቅሰዋል፡፡

የሰማንታ ረዳት ‹‹ለወራት ያህል ነዳጅ፣ ገንዘብ እና የመድኃኒት አቅርቦት በኢትዮጵያ መንግሥት በመታገዱ ምክንያት ሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የሚሰጡትን ድጋፍ ለመቀነስ ተገደዋል። ሆስፒታሎች እና የጤና ተቋማት መድኃኒት አልቆባቸዋል›› ብለዋል።

በየብስ የሚሰጠው የእርዳታ አቅርቦት ካለው የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት አንጻር በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰውም፤ ወደ ትግራይ ክልል ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ አውሮፕላኖች በረራ ቁጥር እንዲጨመርም አሳስበዋል።

የአሜሪካ የተራድኦ ተቋም ባወጣው መግለጫ ረዳት ኃላፊዋ በጦርነቱ ሳቢያ ከተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ተፈናቅለው ባሕር ዳር የሚገኙ ነዋሪዎችን አነጋግረዋል ብሏል። ተፈናቃዮቹ በሞት ስላጧቸው ቤተሰቦቻቸው፣ ምን አይነት ስቃይ እንዳሳለፉ እና ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታም ለሳራ ቻርልስ እንደነገሯቸው ጠቁሟል፡፡

አሁን በህወሓት ቁጥጥር ስር በሚገኙ የአማራ ክልል አካባቢዎች ቤተሰብ ያሏቸው ሰዎች ስለ ቤተሰቦቻቸው ደኅንነት እንደሰጉም ተናግረዋል ነው የተባለው።

በትግራይ ክልል ተነስቶ ወደ አጎራባቾቹ የአማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ አንድ ዓመት የዘለቀው ጦርነት ያስከተለው ሰብአዊ ቀውስ እየተባባሰ መምጣቱን ሳራ ቻርልስ ተናግረዋል።

‹‹ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ በተገቢ ሁኔታ እንዳይደርስ ያለው መሰናክል እንዲሁም በአፋር እና አማራ ክልሎች ተባብሶ የቀጠለው ውጊያ ባለፉት ሳምንታት ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል›› ብለዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሳራ ችርልስ የወከሏት አሜሪካ ለእርዳታ ወደ 663 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንዳወጣች የዩኤስኤድ መግለጫ ይጠቁማል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img