Sunday, September 22, 2024
spot_img

ኦፌኮ በኢትዮጵያ ይካሄዳል የተባለው ብሔራዊ ውይይት የታጠቁ ኃይሎችን ሊያካትት ይገባል አለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 15፣ 2014 ― የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በቅርብ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ብሔራዊ ውይይት የታጠቁ ኃይሎችን ሊያካትት ይገባል ብሏል። ፓርቲው አያይዞ የቡድኖቹን ውክልና ለማንቃትም ሕጋዊ እና የደህንነት መሰናክሎች ከወዲሁ መወገድ አለባቸው ነው ያለው።

ፓርቲው ዛሬ ጥቅምት 15፣ 2014 ከዚህ ቀደም ከብሔራዊ ውይይት ጋር በተገናኝ መካሄድ አለበት በሚል አቋም ሲያንጸባርቅ እንደነበር በማስታወስ፣ አሁን በመንግስት የተያዘው አቋም ከሚቀር ቢዘገይም መምጣቱ መልካም መሆኑን አሳውቋል።

ኦፌኮ በመግለጫው ለብሔራዊ ውይይቱ አራት ቅድመ ሁኔታዎችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ በውይይቱ የታጠቁ አካላት ተሳታፊ መሆን አለባቸው የሚለውን ጨምሮ በአሁኑ እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት በሁሉም አቅጣጫ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የሚካሄደው ብሔራዊ ውይይት በአለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና እና ድጋፍ በተሰጣቸው ወገኖች ሁሉ ተቀባይነት ባለው ገለልተኛ እና ተዓማኒ፣ የማያዳላና በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት ባለው አካል መመራት እንደሚኖርበት እንዲሁም የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ተፈትተው በውይይቱ እንዲሳተፉ ጠይቋል።

በመንግስት በኩል በቅርብ ይካሄዳል ተብሎ የተነገረለት የብሔራዊ ምክክር መድረክ ተሳትፎን በሚመከት እስካሁን ድረስ የጠራ መረጃ የለም። ሪፖርተር ጋዜጣ ትላንት ይዞት በወጣው መረጃ የምክክር መድረክ ላይ የሚሳተፉ አካላት የሚወሰነው በተሳታፊዎች በራሳቸው እንደሚሆን ከሰላም ሚኒስቴር ሰምቻለሁ ብሏል።

ከዚህ ቀደም ብሔራዊ የምክክር መድረኩ በመጪው ኅዳር ወር 2014 እንደሚጀመርና በመድረኩ ላይ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚሳተፉበት መድረኩን እያመቻቸ የሚገኘው ማይንድ ኢትዮጵያ ማሳወቁን የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጥተው ነበር፡፡

ነገር ግን አሁን ሰላም ሚኒስቴር ኅዳር ወር የሚካሄደው ዋናው ብሔራዊ የምክክር መድረክ ሳይሆን ስለመድረኩ ሕዝባዊ ግንዛቤ መፍጠሪያና ማሳወቂያ ውይይት ነው ብሏል።

በዚህ የማስተዋወቂያ ፕሮግራም ላይ የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎችንና ተቋማትን ለሚወክሉ ጥሪ እየተደረገ መሆኑንና እስካሁን ጥሪ ያልደረሳቸው ካሉም በድጋሚ የሚታይ እንደሆነ የሰላም ሚኒስቴር አመልክቷል፡፡

ዋናው ብሔራዊ የምክክር መድረክ መቼ እንደሚካሄድ የሰላም ሚኒስቴር ባይገልጽም፣ በመድረኩ ላይ የሚሳተፉ አካላት የሚወሰነው ግን በራሳቸው በተሳታፊዎቹ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ይካሄዳል ተብሎ እየተጠበቀ የሚገኘውን ብሔራዊ ምክክር መድረክ ከመንግስታዊው የሰላም ሚኒስቴር በተጨማሪ በኢትዮጵያ መንግስት በአዋጅ የተመሰረተው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላትን አካቷል። አጠቃላይ ሂደቱን ከሚያስተባብሩት ውስጥ ከሚገኙት ከስምንቱ የጥምረቱ አባላት መካከል በኢትዮጵያ በህጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ይገኝበታል።

‹‹ማይንድ ኢትዮጵያ›› የተሰኘው ይኸው ጥምረት ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት ያለመ መድረክ ለማካሄድ አቅዶ የነበረው ባለፈው ዓመት 2013 የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት እንደነበር አሳውቋል፡፡ ይህ የጥምረቱ ዕቅድ የተደናቀፈው በዚያው ዓመት በጥቅምት ወር መጨረሻ በትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው ውጊያ ምክንያት እንደሆነ የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪ አቶ ንጉሱ አክሊሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት አዲስ መንግስት የመሠረቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሰላማዊ መንገድ የሚሳተፉ የፖለቲካ ቡድኖችን ያሳተፈ ብሔራዊ ውይይት እንደሚካሄድ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img