አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 15፣ 2014 ― ከትግራይ ክልል ጋር በሚዋሰነው የአፋር ክልል የሕወሃት ኃይሎች መግፋታቸውን ተከትሎ እየተካሄደ በሚገኘው ውጊያ የተፈናቃዮች ቁጥር መበርከቱን የአፋር አርብቶ አደሮች ልማት ማኅበር አስታውቋል፡፡
የልማት ማኅበሩ ባወጣው መረጃ በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ጭፍራ ከተማ ውጊያ ተባብሶ ከቀጠለ 9 ቀናት ማስቆጠሩን የገለጸ ሲሆን፣ የሕወሃት ኃይሎች በዚያው ከተማ ወደ ሦስት ቀበሌዎች በመያዛቸው የተፈናቃዮች ቁጥር እየበረከተ ይገኛል፡፡
ጭፍራ በተባለችው በዚህች ከተማ የሚገኙ በርካታ አካባቢዎች በእሳት መንደዳቸውንም የአፋር አርብቶ አደሮች ልማት ማኅበር ገልጧል፡፡
በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አጎራባች አፋር እና አማራ ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት፣ ለጥቂት ጊዜ ጋብ ያለ ቢመስልም ባለፉት አስር ቀናት በድጋሚ ተባብሶ መቀጠሉ ይነገራል፡፡ በውጊያው የአርብቶ አደር አካባቢ በሆነው አፋር ክልል የሕወሃት ኃይሎች ሰንዝረውታል በተባለ የከባድ መሳሪያ ድብደባ ንጹሐን ሕይወታቸውን መነጠቃቸው መነገሩ የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም የሕወሃት ኃይሎች በንጹሐን ላይ ጥቃት አላደረስንም ሲሉ ሲያስተባብሉ ቆይተዋል፡፡
ይኸው ውጊያ በአማራ ክልል ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች በስፋት እየተካሄደ መሆኑን የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያመለክታሉ፡፡