Saturday, September 21, 2024
spot_img

በሱማሌ ክልል ዕድሜያቸው ለምርጫ ያልደረሰ ሕፃናት ድምጽ ሰጥተዋል ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ጥቅምት 13፣ 2014 ― በሶማሌ ክልል መስከረም 20፣ 2014 በተካሄደው ምርጫ በተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች ዕድሜያቸው ለመምረጥ ያልደረሰ ሕፃናት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀውን የድምጽ መስጫ ወረቀት ይዘው ድምጽ ሲሰጡ ታዛቢዎቹ መመልከታቸውን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ሰብዐዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ነው።

የኢሰመጉ የምርጫ ባለሞያ አቶ ገላውዲዎስ ግሩም ነግረውኛል ብሎ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ እንዳስነበበው፣ በሁለተኛው ዙር ምርጫ ሕፃናት ካርድ ወስደው ድምጽ በመስጠት ሒደቱ መሳተፋቸውን የኢሰመጉ ታዛቢዎች ተመልክተዋል።

ድርጊቱ በሌሎች ምርጫ በተካሄደባቸው አካባቢዎች አልፎ አልፎ ቢኖርም፣ በዋናነት ችግሩ የታየው በሱማሌ ክልል መሆኑን ነው አቶ ገላውዲዎስ የገለጹት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዚህ በፊት በሚያወጣቸው መረጃዎች እና ለመራጮች በሚሰጣቸው ትምህርቶች ድምጽ መስጠት ወይም በምርጫ መሳተፍ የሚችሉት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው ብቻ መሆኑን ገልጿል።

ኢሰመጉ እንደሚለው ከሆነ ችግሩ የተከሰተው በቅድመ ምርጫ ወቅት ሲሆን፣ በምርጫው ለመሳተፍ ምርጫ ካርድ ለመራጮች በሚሰጥበት ጊዜ ያለ አግባብ ዕድሜያቸው ለምርጫ ላልደረሱ ሕጻናት ተላልፎ መሰጠቱ ነው ብሏል።

ኢሰመጉ ምርጫ በተካሄደባቸው ክልሎች በተሳተፈባቸው ምርጫ ጣቢያዎች የታዘባቸው መልካም እና ደካማ ጎኖችን ለምርጫ ቦርድ ሪፖርት ማድረጉም የተገለጸ ሲሆን፣ ጉባዔው ባሰማራባቸው ምርጫ ጣቢያዎች፣ ዕድሜያቸው ለምርጫ ያልደረሰ ሕፃናት በምርጫ መሳተፋቸውን የሚረጋግጡ የምስል ማስረጃዎችን አቅርቧል ነው የተባለው።
ነገር ግን ምርጫ ቦርድ ኢሰመጉ ባቀረበው ጉዳይ ላይ ማብራሪያ አልሰጠም።

የሱማሌ ክልል ከሰኔ 14፣ 2013 ወደ መስከረም 20፣ 2014 የተሻገረው በክልሉ በቅድመ ምርጫ ወቅት በተለይ ከመራጮች ካርድ አሰጣጥ ጋር በተገናኘ አጋጥሟል በተባለው ችግር ነበር።

ምርጫ ቦርድ በክልሉ ያሰራጨው የመራጮች ካርድ በክልሉ ብልጽግና ፓርቲ በኩል ያለ አግባብ መሰራጨቱን በክልሉ ምርጫ የሚሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ አቅርበውበታል።

በክልሉ አጋጥሟል የተባለውን ችግር ምርጫ ቦርድ አጣርቶ ማስተካከያ ማድረጉን መግለጹ የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጂ፣ በክልሉ በተካሄደው ምርጫ ኢዜማ፣ ኦብነግ እና ነእፓን ጨምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አልተሳተፉም። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በክልሉ ምርጫ ያልተሳተፉት በመጀመሪያ ዙር ምርጫ ዝግጅት ላይ አጋጥመዋል ብለው ያቀርቧቸው ችግሮች ባለመስተካከላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ምርጫ ቦርድ በክልሉ መስከረም 20 ያካሄደውን ምርጫ መሠረት አድርጎ የክልሉን ምርጫ አሸናፊ ይፋ አድርጓል። በዚሁ መሠረት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ባሳለፍነው ሳምንት የክልሉን መንግሥት መስርቷል። በዚህም ሙስጠፋ ሙሐመድን የክልሉ ርዕሠ መስተዳድር አድርጎ መርጧል።

አዲስ የተመሰረተው የክልሉ መንግሥት፣ ከምርጫው ራሱን ያገለለውን የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር(ኦብነግ) ሁለት አባላትን በካቢኔው ውስጥ ማካተቱን ገልጿል። ይሁን እንጂ በክልሉ ካቢኔ ውስጥ የተካተቱትን የኦብነግ አባላት ፓርቲው እንደማይወክሉት በይፋዊ ማኅበራዊ ገጹ ባወጣው መረጃ ገልጿል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img