Sunday, September 22, 2024
spot_img

አቶ እስክንድር ነጋ በተፈጸመባቸው ድብደባ የግራ እግራቸው አውራ ጣት መሰበሩን ፓርቲያቸው አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥቅምት 12 2014 ― ከሰሞኑ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ድብደባ እንደተፈጸመባቸው የተነገረው የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ሊቀመንበሩ አቶ እስክንድር ነጋ በድብደባው የግራ እግራቸው አውራ ጣት መሰበሩን ፓርቲያቸው በሕክምና ተረጋግጧል ሲል አስታውቋል፡፡

አቶ እስክንድር የደረሰባቸው ጉዳት እንዲጠግን ለቀጣይ ስድስት ሳምንታት በጀሶ እንደሚቆዩ ያስታወቀው ባልደራስ፣ በሊቀመንበሩ ላይ የተፈመውን ድብደባ ‹‹በእቅድ›› የተደረገ ነው ብሎታል፡፡

ድብደባውን ያስተናገዱት አቶ እስክንድር ነጋ ከማረሚያ ቤት ሆነው አስተላልፈውታል በተባለ መልእክት ‹‹አጥንታችንን መስበር ይቻላል፤ ትግላችንን ግን መስበር አይቻልም›› ማለታቸውም ተመላክቷል፡፡  

የአቶ እስክንድርን ድብደባ በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሚገኙበትን ሁኔታ ለማጣራት ትላንት ጥቅምት 12፣ 2014 በቂሊንጦ ጊዜያዊ ማረፊያ በመገኘት፣ አቶ እስክንድር ነጋን፣ ክስተቱ ሲፈጠር በስፍራው የነበሩትን አቶ ስንታየው ቸኮልን፣ ከአቶ እስክንድር ጋር ተጋጩ የተባሉትን እስረኛ፣ እንዲሁም የማረሚያ ቤቱን አስተዳደር አካላት ማነጋገሩን አስታውቋል፡፡

በማጣራቱ ሂደት አቶ እስክንድር የፍርድ ቤት ቀጠሮ በነበራቸው ሐሙስ ጥቅምት 11፣ 2014 ጠዋት በሚገኙበት ዞን ግቢ ውስጥ የስፖርት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እያሉ፣ ከዚህ ቀደም እርሳቸው ባሉበት ዞን ታስረው የነበሩና ከዞኑ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተዘዋውረው ከነበሩ ከሌላ እስረኛ ጋር ሲገናኙ በመካከላቸው የተነሳው የቃላት ልውውጥ ወደ አካላዊ ግጭት መሸጋገሩን መረዳቱን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ክስተቱ እንደተፈጠረ የእስር ቤቱ ጥበቃዎች እና ሌሎች ታራሚዎች እንዳገላገሏቸውና የማረሚያ ቤቱ አስተዳደርም ሌላኛውን እስረኛ ወዲያው ወደ ሌላ ዞን ማዘዋወሩን ለማረጋገጥ መቻሉንም ጠቁሟል። በአቶ እስክንድር እና በእስረኛው መካከል ከዚህ ቀደም አለመግባባት እንደነበረና እስረኛው ከተዘዋወሩበት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት በቅርቡ የተመለሱ መሆኑንም ኮሚሽኑ መገንዘብ ችያለሁ ብሏል።  

በሁኔታው አቶ እስክንድር በግራ እግር አውራ ጣታቸው ላይ እብጠት፣ በሁለቱም ጉልበቶቻቸው ላይ የመላላጥና በቀኝ ቅንድባቸው ላይ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል ያለ ሲሆን፣ በማረሚያ ቤቱ ክሊኒክ የተመላላሽ ሕክምና እያገኙ መሆኑንና በአሁኑ ጊዜ በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ አረጋግጧል። በሌላኛው እስረኛ ላይም በቀኝ እጅ ጣቶቻቸው ላይ የመፋፋቅ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማየት ማቻሉንም ገልጧል።

ሁለቱም ታሳሪዎች በግጭቱ በደረሰባቸው ጉዳት ተገቢው የማጣራት እና የሕክምና ድጋፍ ከማረሚያ ቤቱ አስተዳደር አካላት እንደተደረገላቸው የገለጹ ሲሆን፣ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ክስ ለመመስረት ፍላጎት እንደሌላቸው አስረድተዋል ነው የተባለው፡፡  

የባልደራስ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ እና ሌሎች የፓርቲው ሰዎች የሓጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከአንድ ዓመት ለተሻገረ ጊዜ በእስር አሳልፈዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img