Sunday, September 22, 2024
spot_img

ሩስያ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ አካላት ያለ ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጠየቀች

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥቅምት 12፣ 2014 ― ሩስያ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ አካላት ያለ ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤቷ በኩል ጠይቃለች፡፡

በጉዳዩ ላይ የተናገሩት የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይዋ ማሪያ ዛካሮቫ በፌዴራል መንግስት እና በሕወሃት ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት ተባብሶ መቀጠሉን መረዳታቸውን ገልጸው፣ አገራቸው ተፋላሚ አካላት ያለ ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ፍላጎቷ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

ሩስያ በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ከባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ወዲህ ወደ አጎራባች አፋር እና አማራ ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት ኢትዮጵያን አስመልክቶ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በሚያካሄዳቸው ስብሰባዎች በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ጎን ስትቆም የቆየች ናት፡፡

አገሪቱ ከቻይና ጋር ባንድነት በመሆን የትግራዩን ጦርነት ለማስቆም በፀጥታው ምክር ቤት ሲደረጉ የነበሩ ጫናዎችን ተቃውማለች።

ሩስያ በጸጥታው ምክር ቤት ባንፀባረቀችው አቋም ከፌዴራል መንግስት በኩል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምስጋና ደብዳቤ የተጻፈላት ሲሆን፣ የመግስት ደጋፊዎችም አገሪቱን አጋርና ወዳጅ አድርጎ በመውሰድ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከቻይና ጋር ሲወደሱ ቆይታለች።

አገሪቱ በጦርነቱ ላይ የአሁን ዐይነት መግለጫ ስታወጣ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ሩስያ ከዚህ ቀደም የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ስምንተኛ ስብሰባውን ሲያደርግ በጦርነት ተፋላሚ አካላት መሃል ውይይት እንዲጀመር ብትጠይቅም፣ ማንኛውም የውጭ ድጋፍ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት፣ የግዛት ምሉእነት ያከበረ እና የፖለቲካ ነጻነትን በጠበቀ መከልኩ እንዲከናወን ጠይቃለች።

በሰሜን ኢትዮጵያ ተባብሶ የቀጠለው ጦርነት በድርድር እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች አገራትም ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡ የአሜሪካ መንግስት ይህ የማይፈጸም ከሆነ በኢትዮጵያ ላይ ማእቀብ ለመጣል በፕሬዝዳንት በኩል ትእዛዝ መፈረሙም አይዘነጋም፡፡ ይኸው ጦርነት ከጀመረ ከአስር ቀናት በኋላ አንድ ዓመት የሚደፍን ሲሆን፣ በጦርነቱ የበርካቶች ሕይወት ሲቀጠፍ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ኢትዮጵያውያን ደግሞ አፈናቅሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img