አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥቅምት 12፣ 2014 ― የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የሰብአዊ እርዳታ የጫነ አውሮፕላን በዛሬው እለት መንግስት ባካሄደው የዐየር ጥቃት ምክንያት መቀሌ ማረፍ ሳይችል መቅረቱን ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
የዜና ወኪሉ ሁለት የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞችን ጠቅሶ እንዳሰፈረው፤ አውሮፕላኑ መቀሌ ማረፍ ስላልቻለ ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል፡፡
ሆኖም ጉዳዩን በተመለከተ የተናገሩት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ‹‹በራሳቸው ምክንያት ካሆነ በስተቀር የአየር ድብደባው እና የሰብአዊ እርዳታ ጫኝ አውሮፕላን እንቅስቃሴ አይገናኝም›› ማለታቸውን አል ዐይን አስነብቧል፡፡
ሰዓቱ የተለያየ መሆኑን የገለጹት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ፤ ‹‹መዳረሻዎችም የተለያዩ ናቸው›› ማለታቸው ተመላክቷል፡፡
መንግስት በአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማጣሪያ ዛሬ ገጹ ባወጣው መግለጫ በዛሬ እለት ‹‹የአሸባሪው የህወሓት ማሰልጠኛ ማዕከል ዛሬ የአየር ጥቃት ዒላማ ሆኗል›› ብሏል። ማዕከሉ ለሕወሃት ወታደራዊ ሥልጠና ከመዋሉ በፊት የኢፌዴሪ መከላከያ ማሠልጠኛ ማዕከል እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡
በዛሬ እለት በኢትዮጵያ አየር ኃይል በሳምንቱ ለአራተኛ ጊዜ የተፈጸመው የአየር ድብደባ ንጹሐንን ለጉዳት ዳርጓል በሚል ሕወሓት በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሃን ቢዘገብም፣ ሌሎች ምንጮች እስካሁን ያወጡት መረጃ የለም፡፡