አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥቅምት 12፣ 2014 ― የፌዴራል መንግሥት በዛሬው እለት የሕወሓትን ማሰልጠኛ ማእከል ኢላማ ያደረገ የአየር ላይ ጥቃት እንደተፈጸመ አስታውቋል፡፡
መንግስታዊው የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ገጽ እንደገለጸው፣ ማእከሉ ለሕወሃት ወታደራዊ ሥልጠና ከመዋሉ በፊት የኢፌዴሪ መከላከያ ማሠልጠኛ ማዕከል ነበር። ይኸው ማእከል ከወታደራዊ ስልጠና በተጨማሪ የውጊያ ግንኙነት ኔትወርክ ያለበት ነው ተብሏል፡፡
በዛሬ እለት በኢፌዴሪ አየር ኃይል ጥቃት የተሰነዘረው ወደ መቐለ ከተማ መሆኑን የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ነግረውኛል ብሎ ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡ የዜና ወኪሉ አቶ ጌታቸው ዝርዝር ጉዳዮችን አለመናገራቸውን በዘገባው አስፍሯል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከሰኞ ጥቅምት 8፣ 2014 አንስቶ ወደ መቐለ ጥቃት ሲሰነዝር የዣሬው ለአራተኛ ጊዜ ነው፡፡