Sunday, September 22, 2024
spot_img

ፌስቡክ ‹የኦሮሞ ነጻነት ጦር› የተባለውን ታጣቂ ቡድን ከገጹ አገደ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥቅምት 12 2014 ― የዓለማችን ግዙፉ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ የሆነው ፌስቡክ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለውን ታጣቂ ቡድን ከገጹ ማገዱ ተነግሯል፡፡ ኩባንያው ታጣቂ ቡድኑን ያገድኩት ‘አደገኛ ድርጅቶች’ በሚለው መመሪያው መሠረት እንደሆነ አሳውቆኛል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ በሚል የተፈረጀው ቡድኑ፣ በምዕራብ፣ በመካከለኛው እና በደቡብ ኦሮሚያ ክልል የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደረግ መሆኑን የሚናገር ነው፡፡  

ፌስቡክ ከቀናት በፊት ይፋ በተደረገበት ምስጢራዊ የተባለው የጥቁር መዝገብ ሰነድ ላይ ቡድኑን መንግሥታዊ ያልሆኑ ሁከት ፈጣሪ አካላት (ቫዮለንት ነን ስቴት አክተርስ) የሚለው ዝርዝር ውስጥ አካቶታል፡፡

የኦሮሞ ነጻነት ጦር ከፌስቡክ በመታገዱ በኦሮሞ ነጻነት ጦር ወይም ጦሩን ወክለው የሚከፈቱ ወይም የተከፈቱ የፌስቡክ አካውንቶች አይኖሩም ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ለቡድኑ ድጋፍ የሚሰጥ ወይም ቡድኑ የሚፈጥረውን ሁከት የሚያወድስ ይዘት›› እንደማይፈቅድ ፌስቡክ አሳውቋል፡፡

የፌስቡክ ቃል አቀባይ ኩባንያው ድርጅቶችን በተለያየ ጎራ ከመፈረጁ በፊት ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ባለሞያዎች ጋር ዝርዝር ሥርዓቶችን እንደሚከተል ገልጸዋል።

ቢቢሲ የፌስቡክን ውሳኔ ተከትሎ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ቃል አቀባይ ነው የተባለውን ግለሰብ አስተያየት ጠይቄ ፌስቡክ በቡድኑ ላይ የወሰደውን እርምጃ እንደሚያውቅ ገልጾልኝ፣ ውሳኔው በተለያዩ ቡድኖች ‹‹የኦሮሞ ሕዝብን እና ሌሎች የተጨቆኑ ቡድኖችን ድምጽ ለማፈን›› በተካሄደ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተጽእኖ ነው ብሎኛል ሲል አስፍሯል፡፡

ጨምሮም በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ሌሎች ‹‹የሰብአዊ መብት ጥሰትና ጭፍጨፋዎች የፈጸሙና ማስረጃ የሚቀርብባቸው ቡድኖች›› በነጻነት ፌስቡክን እየተጠቀሙ የኦሮሞ ነጻነት ጦርን በመሠረተ ቢስ ፕሮፓጋንዳ ማገድ ‹‹የፌስቡክን ፖሊሲ ማን ተጽእኖ እያደረገበት እንደሆነ ግልጽ ነው›› ማለቱም ተመላክቷል፡፡

የፌስቡክ ቃል አቀባይ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ከኩባንያው መመሪያ በተቃራኒ የተለያዩ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ሌሎች በርካታ ቡድኖችና ግለሰቦች መንግሥታዊ ባልሆኑ ሁከት ፈጣሪ አካላት ወይም በሌሎች ዘርፎች ውስጥ ተካተው እገዳ እንደተጣለባቸው ገልጸዋል፡፡

ፌስቡክ አደገኛ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ፖሊሲ አሸባሪ ድርጅቶችን፣ የጥላቻ ቡድኖችን እና የወንጀል ድርጅቶችን ጨምሮ የተለያዩ አካላትን የሚመለከት ፖሊሲ እንዳለው ይነገራል፡፡ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ሲል የሚጠራው ቡደን የተካተተበት መንግሥታዊ ያልሆኑ ሁከት ፈጣሪ አካላት (ቫዮለንት ነን-ስቴት አክተርስ) የሚለው ዝርዝር በአጠቃላይ ንጹሃንን ዒላማ የማያደርጉ ነገር ግን በመንግሥት እና በጦር ሠራዊት ላይ ሁከት የሚፈጥሩትን የሚያካትት መሆኑ ተገልጧል፡፡

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለውና በመንግስት ሸኔ የሚባለው ቡድን፣ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚደርሱ የንጹሐን ጥቃቶች በመንግስት ውንጀላ የሚቀርብበበት ነው፡፡ ቡድኑ በቅርቡ ከሌላኛው በሽብረተኝነት ከተፈረጀው ሕወሃት ጋር አብሮ ለመስራት መስማማቱ መነገሩ አይዘነጋም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img