Monday, November 25, 2024
spot_img

በሶማሌ ክልል የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለጸ

ከመሀል አገር በሶማሌ ክልልን አቋርጦ ወደ ጎረቤት አገሮች የሚጓጓዝ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ረዳት ኮሚሽነር መሐመድ አሊ እንደገለጹት ባለፉት ሦስት ዓመታት ከደቡብ ክልልና ከመሀል አገር ተጭኖ ወደ ጎረቤት ኬንያ፣ ሶማሊያና ሌሎች መዳረሻ አገሮች ሊጓዝ ሲል በቁጥጥር ሥር የሚውለው የአደንዛዥ ዕፅ መጠን ተበራክቷል፡፡

ኮሚሽነሩ አጠቃላይ የክልሉን የፀጥታ ጉዳይ አስመልክተው ማክሰኞ ጥቅምት 9፣ 2014 በጅግጅጋ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በየቀኑ በመኪና ተጭኖ ከአገር ሊወጣ ሲል የሚያዘው የዕፅ መጠን ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ እየጨመረ በመጣው የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ክልሉ እየተቸገረ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ‹‹በጣም ብዙ ወንጀለኞችን ብንይዝም ዝውውሩ ሊቆም አልቻለም፣ ዕልባትም አልተገኘለትም፤›› ብለዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም ከፌዴራል ፀረ ኮንትሮባንድ ግብረ ኃይል ጋር በመሆን በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም፣ ክልሉ ካለው የቆዳ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር አለመቻሉን ነው የገለጹት፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሶማሌ ክልል ካለው የቆዳ ስፋት አንፃር በኢትዮጵያ አጎራባች አገሮች አካባቢ የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን፣ በጉጂ ዞን ቦረናና ባሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው በአሸባሪነት የተሰየመው የኦነግ-ሸኔ እንቅስቃሴ ለክልሉ ሥጋት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የአገር መከላከያ ሠራዊት ከሕወሓት ጋር እያደረገ ባለው ውጊያ ሳቢያ በድንበር አካባቢ ከአልሸባብ ሊመጡ የሚችሉ ጥቃቶችን ለመመከት፣ በሶማሌ ክልል የፀጥታ ኃይሎች አማካይነት ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽነር መሐመድ አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ውስጥ ከገባ ጀምሮ ሶማሌ ክልልን አቋርጠው የሚጓዙ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ቁጥር መቀነሱን ገልጸው፣ ይሁን እንጂ አሁንም የሶማሌ ክልልን አቋርጠው በሕገወጥ መንገድ ወደ ሩቅ ምሥራቅ አገሮች ለመውጣት የሚሞክሩት ሰዎች በአመዛኙ ከሳዑዲ ዓረቢያ የተመለሱና በድጋሚ ለመሄድ የሚሞክሩና በአብዛኛው ከአማራ፣ ከኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡
ለአብትም በቅርቡ ድንበር አቋርጠው ሶማሌላንድ ግዛት ውስጥ ገብተው በቁጥጥር ሥር የዋሉ 106 ዜጎችን ወደ አገራቸው መመለስ መቻሉን አስታውቋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img