አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 10፣ 2014 ― በምሥራቃዊ የሜዲትራኒያን ጫፍ ላይ በምትገኘው የምዕራብ እስያ አገር በሆነችው ሊባኖስ ለሥራ በሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን ላይ ከፍተኛ በደል እንደሚደርስ አልጀዚራ ይዞት በወጣው ዘለግ ያለ ዘገባ አመልክቷል፡፡
እነዚህ ኢትዮጵያውያን በብዛት በቤት ሠራተኛነት እና ተዛማጅ ሥራዎችን ለመሥራት ወደ አገሪቱ የሚሄዱ መሆናቸውን ያመለከተው ዘገባው፣ ነገር ግን እዚያ ከደረሱ በኋላ አንዳንዶቹ አሠሪዎቻቸው የግንኙነት መስመራቸውን በመቁረጥ ያለ ደመወዝ ለረዥም ዓመታት እንዲሠሩ እንደሚያስገድዷቸውም አስፍሯል፡፡
በአሰሪዎቻቸው ስፖንሰር አድራጊነት ወደ አገሪቱ የሚጓዙት እነዚሁ ኢትዮጵያውያን፣ ሊባኖስ ከደረሱ በኋላ አሠሪዎቻቸው ፓስፖርታቸው እንደሚቀሟቸው፣ ለረዥም ሰአት ያለ እረፍት እንደሚያሰሯቸው፣ የእረፍት ቀን ፍቃድ እንደማይሰጧቸው፣ መንቀሳቀስ እና ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኙ የግንኙነት መስመሮችን እንደሚዘጉባቸው ነው የተነገረው፡፡
ዘገባው ወደ ሊባኖስ ለሥራ አቅንተው በአሠሪዎቻቸው ከላይ የተጠቀሱ በደሎች የደረሰባቸውን ኢትዮጵያውያን ሴቶች እና አድራሻቸውን ማግኘት ያልቻሉ ቤተሰቦቻቸውን ሰቆቃ በተንቀሳቃሽ ምስል እና በፎቶግራፍ አያይዞ አውጥቷል፡፡
ኢትዮጵያውያኑን ከአገር ቤት ወደ ሊባኖስ በሕገ ወጥ መንገድ ለማዘዋወር በአገሪቱ የሚገኙ ኤጀንሲዎች አገር ቤት ከሚገኙት ጋር ጥምረት በመፍጠር እንደሚሠሩ የተዘገበ ሲሆን፣ ይህንኑ ለማስፈጸም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ኤጀንሲዎች እስከ 500 ዶላር የሚገመት ገንዘብ እንደሚያስከፍሉና ሠራተኞቹም በሊባኖስ በወር 150 ዶላር ገንዘብ በአማካይ እንዲከፈላቸው ተስማምተው ይሄዳሉ ነው የተባለው፡፡
ሆኖም እዚያ ሲደርሱ ይህ ስምምነት ተፈጻሚ እንደማይሆን ለስምንት ዓመት በአገሪቱ ቆይታ አሰሪዋ ስባሪ ሳንቲም ሳትሰጣት የሸኘቻት እመቤት ዓለሙ በተባለች ኢትዮጵያዊት ታሪክን አልጀዚራ በማሳያነት አቅርቧል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ሊባኖስ በሠራተኝነት የሚጓዙ ዜጎቿ ላይ የሚደርሰውን ከፍተኛ በደል የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ተከትሎ በ2001 ወደ አገሪቱ የሚደረግ የሰራተኞችን ጉዞ እገዳ ብትጥልም እግዱ በትክክል ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቶ አሁንም ዜጎች መንገላታታቸውን እንደቀጠለ ዘገባው አመልክቷል፡፡