Wednesday, October 9, 2024
spot_img

ኔዘርላንድ ከቃሊቲ እስር ቤት ያመለጠው በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎች አዘዋዋሪው ኪዳኔ ዘካርያስን በጥብቅ ከሚፈለጉ ዝርዝር አካተተች

 

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 10 2014 ― የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ ኤርትራዊውን በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪነት የሚፈለገውን ኪዳኔ ዘካርያስ ሀብተማርያምን በሕግ በጥብቅ ከሚፈለጉ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ማካተቱ ተሰምቷል፡፡

ኪዳኔ ዘካርያስ ሀብተማርያም በሰዎች ግድያ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ መጠቀም በሚል በርካታ ክሶች የሚቀርብበት ነው፡፡

ኪዳኔ በአዲስ አበባ ለአንድ ዓመት ገደማ የሁለት ስደተኞች ግድያን ጨምሮ በስምንት ሰዎች ዝውውር ተከሶ የፍርድ ሂደቱን እየተከታተለ ሳለ ማምለጡ ይነገራል፡፡ ኪዳኔ ከእስር ቢያመልጥም ፍርድ ቤቱ በሌለበት የእድሜ ልክ እስራት የፈረደበት ሲሆን፣ አሁን ግን የት እንዳለ በትክክል አይታወቅም።

ግለሰቡ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በሌለበት የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ወደ አውሮፓ ለመሄድ ሊቢያ ውስጥ የሚጠባበቁ አፍሪካውያን ስደተኞችን በማስራብ፣ በማሰቃየት እና በማንገላታት ክሶች ነው።

ትውልደ ኤርትራውያን የሕግ ባለሞያዎችን ጨምሮ ብዙ የሌሎችም አገራት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ግለሰቡ ለፍርድ እንዲቀርብ በተለያየ ጊዜያት ጥሪ አቅርበዋል።

ሕገ ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪው በሌለበት እድሜ ልክ ሲፈረድበት፣ በእርሱ ስም ገንዘብ በመቀበል አብራው የተከሰሰችው ሳባ መንድር ኃይሌ የ12 ዓመት እስር ተፈርዶባታል። ሌላው የእሱ ተባባሪ እንደሆነ የሚነገረው እና ዋሊድ በሚል ስም የሚታወቀው ተወልደ ጎይቶም በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የ18 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።

ቢቢሲ አይሪሽ ታይምስን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፣ እአአ ከ2014 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት ኪዳኔ እና ተወልደ በ10 ሺሕዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ሊቢያ ውስጥ አዘዋውረዋል።

የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ ከጣልያን ጋር በመተባበር ኪዳኔን ይዞ ለፍርድ እንደሚያቀርበው አስታውቋል።

ኪዳኔ ዘካሪያስ ‹‹የዓለማችን እጅግ አደገኛ እና ጨካኝ ሰው አዘዋዋሪ›› በሚል በተደጋጋሚ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ይገለጻል። ሊቢያ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች የሚገኙበት ካምፕ እንዳለውም ይነገራል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img