Monday, November 25, 2024
spot_img

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የሕወሓት ኃይሎች የትግራይን ድንበር ተሻግረው የያዟቸውን አካባቢዎች ለቀው ካልወጡ የእርዳታ ተደራሽነትን ማቅለል እንደማይቻል መናገራቸውን ብሉምበርግ ዘገበ

  • – ሕወሓት ለጥያቄው ምላሽ ሰጥቷል

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 10፣ 2014 ― ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህን ተናግረዋል የተባለው ባለፈው ዐርብ ጥቅምት 5፣ 2014 ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ ጋር የስልክ ቆይታ ባደረጉበት ወቅት መሆኑን ነው ብሉምበርግ የዘገበው፡፡  

ከትግራይ ክልል ድንበር ተሻግሮ አጎራባች የአማራ ክልል አካባቢዎችን የያዘው ሕወሓት በበኩሉ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉን ዘገባው ሁለት ሥማቸውን ያልጠቀሳቸውን ዲፕሎማቶች ዋቢ አድርጎ አስፍሯል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቧል የተባለውን ጥያቄ ውድቅ ያደረገው ሕወሓት፣ በአንጻሩ የኤርትራን ጦር ለቆ መውጣት ጠይቋል ነው የተባለው፡፡

አንድ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ሳምንታት የቀሩት በሰሜን ኢትዮጵያ በፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት መካከል የሚካሄደው ጦርነት ከሰሞኑ ማገርሸቱ በስፋት እየተነገረ ይገኛል፡፡ በዚሁ ጦርነት ወደ አጎራባች አማራ እና አፋር የገፋው ሕወሓት ባለፈው እሑድ የውጫሌ ከተማን ተቆጣጥሮ እንደነበር የተነገረ ቢሆንም፣ የፌዴራል መንግስት ኃይሎች በድጋሚ ማስለቀቃቸውን የዶይቸ ቬለ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከትላንት በስትያ ሰኞ ጥቅምት 8፣ 2014 ወደ መቐለ የአየር ላይ ጥቃት መሰንዘሩ መነገሩ አይዘነጋም፡፡  

ጦርነቱን በተመለከተ ከጥቂት ቀናት በፊት ለኒውዮርክ ታይምስ የተናገሩት የሕወሃት ጦር አዛዥ ጀኔራል ጻድቃን ገብረትንሳይ ‹‹በቀናት ወይም በሳምንታት ይጠናቀቃል›› ባሉት ውጊያ፣ ጎረቤት አገር ኤርትራ ትልቅ ወታደራዊ ስጋት እንደሆነችባቸው በመጥቀስ፣ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ኤርትራን እንዲያስታግስላቸው ጠይቀው ነበር፡፡

በዚህ ጦርነት ላይ የኤርትራ ጦር ከዚህ ቀደም ተሳትፎ እንደነበረው በይፋ ሲነገር ቢቆይም፣ በቅርብ ሳምንታት የጦሩን ተሳትፎ በተመለከተ ይፋዊ መረጃዎች አልወጡም፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በርካታ ንጹሀንን ስቃይ ውስጥ መጣሉን የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ሲናገሩ ይሰማል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቅርብ ጊዜያት በተለይ የትግራይ ክልል ይፋዊ ባልሆነ የሰብአዊ እርዳታ እገዳ ስር ይገኛል በሚል በመንግስት ላይ ቅሬታውን ሲያቀርብ ነበር፡፡ የድርጅቱ የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ የኢትዮጵያ መንግሥት የእርዳታ አቅርቦት የያዙ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዲገቡ እንዲያደርግ ጠይቀው፣ ችግሩንም ‹‹ሰው ሰራሽ ነው፣ መንግሥት እርምጃ ከወሰደ መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል›› ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረው ነበር፡፡

በመንግስት በኩል ከዚህ ቀደም ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ጭነው ከተጓዙ 590 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች መካከል 428 የሚሆኑት ከክልሉ አለመመለሳቸውን ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡ መንግስት በክልሉ የሰብአዊ አቅርቦትን ለማዳረስ ሲል የፍተሻ ጣቢያዎቹንም ከሰባት ወደ ሁለት መቀነሱንም አሳውቋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት በድርድር እንዲፈታ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረትን የመሳሰሉ አካላት ጫና እያሳደሩ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img