አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥቅምት 9፣ 2014 ― በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ 50 ኢትዮጵያውያን ዜጎችን በማገትና በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተጠረጠረው ግለሰብ ፍርድ ቤት መቅረቡ ተሰምቷል፡፡
የ50 ዓመቱ አሕመድ ካፌቾ ባለፈው ሳምንት ከ 12 እስከ 50 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 50 ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ዘካሪያ በተባለ መናፈሻ ውስጥ በማገትና ታጋቾቹ እንዲለቀቁ ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ በመጠየቅ ወንጀል ነበር በቁጥጥር ስር የዋለው።
የአገሪቱ ብሔራዊ ዓቃቤ ሕግ ቃል አቀባይ ከእገታው የተረፉት ሰዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዴት እንደገቡና በአገሪቱ ውስጥ ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ከሀገር ውስጥ ጉዳይ መምሪያ ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
ለተጨማሪ ምርመራ ችሎቱ እስከ ጥቅምት 15፣ 2014 ድረስ እንዲዘገይ መደረጉን መግለጻቸው አይ ኦ ኤል የተባለው ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡
ከታገቱት ዜጎች ቤተሰቦች ጋር በቀጥታ የተገናኘ መሆኑንና ታጋቾቹም የት እንደሚገኙ መረጃ ማቀበሉን ያካባቢው ፖሊስ ገልጿል።
ደቡብ አፍሪካ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሕገ ወጥ መንገድ ስደት የሚሄዱባት መሆኗ ይታወቃል፡፡