Sunday, September 22, 2024
spot_img

ሕወሓት ንጹሐንን ኢላማ ያደረገ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ከፍቷል ሲል የአፋር ክልል አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥቅምት 8፣ 2014 ― የአፋር ክልላዊ መንግስት ሕወሓት ከሰሞኑ የክልሉ አካባቢዎች በሆኑት በበራህሌ፣ በመጋሌ፣ በኡዋ እና በጭፍራ በኩል ከርቀት ከባድ መሳሪያ ንጹሐንን ኢላማ ያደረገ ተኩስ መክፈቱን አስታውቋል፡፡

በክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ በኩል በወጣው መግለጫ፣ ሕወሀት በጥቃቱ ሕጻናት እና ሴቶችን እንዲሁም አዛውንቶችን ኢላማ ከማድረግ ባሻገር፣ የአፋር አርብቶ አደር የኢኮኖሚ መሰረት የሆኑትን ግመል፣ ከብት እና ፍየሎች ጭምር በከባድ መሳሪያ በመደብደብ ህዝቡ ላይ የሚደርሰው ጉዳት እጥፍ ድርብ እንዲሆን በማድረግ ላይ ይገኛል ሲል ከሷል፡፡

የአፋር ክልል ሕወሃት ከሰሞኑ አድርሶታል ያለውን ጥቃት ቡድኑ ‹‹ከዚህ ቀደም በአፋር በፈንቲ ረሱ በኩል እና በኪልበቲ ረሱ ዞኖች በኩል ከአሁን በፊት ያደረገውን ወረራ የአፋር ልዩ ሀይል፣ ሚሊሺያ እና ህዝባዊ ሰራዊት በሚገባ በመመከት ወደ መጣበት በመመለስ የደረሰበትን ኪሳራ ለመሸፈን በሚመሰል መልኩ›› ያደረገው ነው ብሎታል፡፡  

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀውና ከፌዴራል መንግስት ጋር ውጊያ ውስጥ የሚገኘው ሕወሃት ከዚህ ቀደም በአፋር ክልል ጋሊኮማ ሰንዝሮታል በተባለው ጥቃት ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ንጹሐን ሲገደሉ፣ ብዙ ሺሕ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎችን መፈናቀላቸው በወቅቱ ተነግሮ ነበር፡፡

የአፋር ክልል ካወጣው መግለጫ ቀድሞ ከቀናት በፊት በፌዴራል መንግሥት አዲስ ጥቃት እየተሰነዘረባቸው መሆኑን ሲያሳውቁ የሰነበቱት የሕወሃት ኃይሎች፣ በአፋር ክልል አውራ ከተማ ሰንዝረውታል በተባለ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ንጹሐንን ኢላማ አድርገው በርካታ ሰዎች መግደላቸውን የፈረንሳዩ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ የረድኤት ድርጅቶችን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በፈንቲ ዞን በምትገኘው አውራ ከተማ የሕወሓት ኃይሎች ጥቃቱን ሰንዝረውታል የተባለው ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ቀናት ነበር፡፡ የአፋር ክልል መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ መሐመድ አሕመድ ለመገናኛ ብዙኃን እንዳሉት ተፈጽሟል በተባለው በዚሁ የከባድ ጦር መሣሪያ ጥቃት የ6 እና የ9 ዓመታት ዕድሜ ያላቸው ሕጻናትን ጨምሮ የሰባት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 15 ሰዎች ላይ ደግሞ አስከፊ የተባለ ጉዳት ደርሷል፡፡

ነገር ግን የከባድ መሳሪያ ጥቃቱን ሰንዝሮ ንጹሐንን ገድሏል የተባለው ሕወሃት ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ በአካባቢው በንጹሐን ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ሰንዝረዋል መባሉን አስተባብለዋል፡፡ አቶ ጌታቸው ውንጀላውን ‹‹የኛን ኃይሎች ለማራከስ የሚደረግ ነው›› ብለውታል፡፡

ከቀናት በፊት ሕወሓት በመከላከያ ከባድ የማጥቃት ጥቃት እየተሰነዘረብኝ የሚል መገለጫ ያወጣ ቢሆንም፣ ዘግየት ብሎ ሌላ መግለጫ ያወጣው የመከላከያ ሚኒስቴር ጥቃቱን ከጥቅምት 1፣ 2014 አንስቶ ያስጀመረው ራሱ ሕወሃት ነው ብሏል፡፡

ባለፉት ቀናት አገርሽቷል የተባለው በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ውጊያ ከአፋር ውጪ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ወልድያ ከተማ አቅራቢያም እየተካሄደ መሆኑን የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ሳምንታት የቀሩት በፌዴራል መንግስት እና በሕወሃት መካከል የሚካሄደው ጦርነት የበርካቶችን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ ሌሎችን ለረሐብ መጣሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተደጋጋሚ ይገልጻል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img