Monday, September 23, 2024
spot_img

በቴሌና በሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ተይዘው ሥራ ላይ ያልዋሉ ቦታዎችን ለቤት ልማት ሥራ ለማዋል እንቅስቃሴ መጀመሩ ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ጥቅምት 7፣ 2014 ― በፌዴራልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ባሉ በቴሌና በሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት የተያዙ ክፍትና ሥራ ላይ ያልዋሉ ቦታዎች፣ ለቤቶችና ሌሎች ልማት እንዲውሉ የተቀመጠውን አቅጣጫ ተግባራዊ ማድረግ እንደተጀመረ ተነግሯል፡፡

መስከረም 24፣ 2014 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አዲስ ለተቋቋመው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተነሱ ጥያቄዎችን ሲመልሱ እንደገለጹት፣ በመንግሥት ተቋማት የተያዙ መሬቶች ለአገልግሎት ሳይውሉ፣ በአንጻሩ ዜጎች በመኖሪያ ቤት እጥረት መሰቃየታቸው ከሀብት አስተዳደር አንጻር ያለውን ክፍተት በግልጽ ያሳያል፡፡

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳነሱት በአዲስ አበባ፣ በቦሌና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍላተ ከተሞች ብቻ በድምሩ 600 ቢሊዮን ብር የሚገመት መሬት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያለአግባብ ተይዟል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ጥራቱ በየነ እንዳስታወቁት፣ በመንግሥት የተያዙ መሬቶች ለልማት እንዲውሉ በማሰብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በፓርላማ የተቀመጠውን አቅጣጫ መሠረት በማድረግ፣ የከተማ አስተዳደሩ በፌዴራልም ሆነ በከተማው አስተዳደር በሚገኙ ተቋማት ተይዘው የሚገኙ መሬቶች፣ በቀጣይ አሠራሩን ተከትሎ ለከተማው ነዋሪዎች የቤት ልማት አገልግሎትና ለሌሎች መሠረተ ልማቶች እንዲውሉ የማድረግ አቅጣጫን ተከትሎ እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በዚህ ወቅት አቅጣጫውን ተከትለው የወጡ ሥራዎች እንደተጀመሩ የተጠቀሰ ሲሆን፣ የተጀመረው ሥራ ሲጠናቀቅ ምን ያህል መሬት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ለልማት እንደዋለና ከመንግሥት ተቋማት ወደ ሕዝብ መጠቀሚያነት እንደተቀየረ መረጃው በቀጣይ ይፋ እንደሚደረግ አቶ ጥራቱ ገልጸዋል፡፡

አቶ ጥራቱ በየነ በመንግሥታዊ ተቋማት ሥር ያሉ ይዞታዎችን ወደ ሕዝብ ይዞታነት የማስተላለፍ ሒደቱ በተጨባጭ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img