አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ጥቅምት 6፣ 2014 ― አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሕገ መንግሥት ረቂቅን አስመልክቶ በቤንች ሸኮ ዞን ከሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እያደረገ ይገኛል፡፡
የክልሉ ህገ መንግስት በ11 ምዕራፍና በ124 አንቀጾች የተዋቀረ መሆኑ በመድረኩ በመድረኩ የተገለጸ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አዲስ ህገ መንግስት ረቂቅ ላይ በዳውሮ ዞን ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
ለአዲሱ ክልል የተቀረፀው ህገ መንግስት በሀገሪቷ ህገ-መንግስት እና የሌሎች ክልሎች ተሞክሮ በመቀመር የተዘጋጀ መሆኑ ሲገለጽ፣ በህገ-መንግስት ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ብርሃኑ አታሮ የልማትና የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲቻል የተመሠረተው አዲሱ ክልል የክልሉ የስራ ቋንቋ አማርኛ እንሚሆንና ሌላው የክልሉ አካባቢዎች ቋንቋ በምክር ቤት ይሁንታ ካገኝ ሊወሰን እንደሚችል በህገ መንግስቱ መካተቱን አሳውቀዋል።
ለአዲሱ ክልል የተዘጋጀው ይህ ህገ-መንግስት የክልሉን ብሔራዊ መዝሙር፣ ስደቅ አላማና የመሳሰሉትን ያካተተ ሲሆን፣ ለውይይት ቀርቦ ሀሳብና አስተያየት ይሰጥበታል ተብሏል፡፡
የአዲሱ ክልል ሕዝበ ውሳኔ ጽ/ቤት ኃላፊ ኢንጅነር ምትኩ በድሩ በበኩላቸው፣ የክልሉ መቀመጫን በሚመለከት በአንድ ማዕከል እንደማይሆንና ይህም በፊት ሲቀርብ የነበረው አንድ ከተማን ብቻ የማሳደግ ችግርን የሚፈታ ነው ማለታቸውን የደቡብ ክልል ሬድዮና ቴሌቪዥን ዘግቧል።
አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የኢትዮጵያ 11ኛ ክልል ሆኖ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በቅርቡ በይፋ ይመሰረታል ተብሎ ይጠበቃል።