Sunday, November 24, 2024
spot_img

የሕወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል አውራ ከተማ ሰንዝረውታል በተባለ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ንጹሐን ኢላማ መደረጋቸው ተዘገበ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 4፣ 2014 ― ከባለፈው ሳምንት መገባደጃ ቀናት አንስቶ በፌዴራል መንግሥት አዲስ ጥቃት እየተሰነዘረባቸው መሆኑን በቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ የገለጹት የሕወሃት ኃይሎች፣ በአፋር ክልል አውራ ከተማ ሰንዝረውታል በተባለ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ንጹሐንን ኢላማ አድርገው በርካታ ሰዎች መግደላቸውን የፈረንሳዩ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ የረድኤት ድርጅቶችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

በፈንቲ ዞን በምትገኘው አውራ ከተማ የሕወሓት ኃይሎች ጥቃቱን ሰንዝረውታል የተባለው ከትላንት በስትያ ማክሰኞ ጥቅምት 2፣ 2014 ነው፡፡ ነገር ግን ጥቃቱን ሰንዝሮ ንጹሐንን ገድሏል የተባለው ሕወሃት ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ በአካባቢው ያገረሸ ውጊያ መኖሩን አረጋግጠው፣ በንጹሐን ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ሰንዝረዋል መባሉን ግን ማስተባበላቸው በዘገባው ተመላክቷል፡፡ አቶ ጌታቸው ውንጀላውን ‹‹የኛን ኃይሎች ለማራከስ የሚደረግ ነው›› ብለውታል፡፡

ጌታቸው የሰሜኑ ጦርነት ወደ አፋር ክልል ተዛምቶ ሐሮ እና ጭፍራ በተባሉ አካባቢዎች ውጊያ እየተደረገ መሆኑን ሌላኛው የኔና ወኪል ሬውተርስም ነግረውኛል ብሎ የዘገበ ቢሆንም፣ በንጹሐን ደርሷል የተባለውን ጥቃትም ሆነ ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ እስካሁን ድረስ የአፋር ክልል ያለው ነገር የለም፡፡

ባለፉት ቀናት አገርሽቷል የተባለው በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ውጊያ ከአፋር ውጪ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ወልድያ ከተማ አቅራቢያም እየተደረገ መሆኑን ከሕወሃት በኩል እየተነገረ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ሰሞኑን ስላገረሸው ውጊያ ያለው ነገር የለም።  በዚህ ዙር ውጊያ የኤርትራ ወታደሮች በአፋር ክልል በርሃሌ ከተማ አቅራቢያ እየተሳተፉ እንደሚገኙም የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ሳምንታት የቀሩት በፌዴራል መንግስት እና በሕወሃት መካከል የሚካሄደው ጦርነት የበርካቶችን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ ሌሎችን ለረሐብ መጣሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተደጋጋሚ ይገልጻል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img