Monday, November 25, 2024
spot_img

‹የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት› በፌስቡክ የአደገኛ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጥቁር መዝገብ ውስጥ መካተቱ ይፋ ሆነ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥቅምት 4፣ 2014 ― ‹የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት› በሚል ራሱን የሚጠራውና በመንግስት ‹ኦነግ ሸኔ› የሚባለው ታጣቂ ቡድን በፌስቡክ የጥቁር መዝገብ መካተቱ ይፋ ሆኗል፡፡ ግዙፉ የዓለማችን የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ፌስቡክ አደገኛ ያላቸውን ግለሰቦችና ድርጅቶችን የያዘበት ምስጢራዊ ሰነድ ይፋ ሲደረግ በበርካታ አገራት የሚገኙ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሥም ተካቶበታል፡፡

ከኢትዮጵያ በብቸኝነት የተካተተው ‹የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት› ቡድን በኩምሳ ድሪባ ወይም ጃል መሮ እንደሚመራ የሚነገር ሲሆን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር በሽብርተኝነት የፈረጀው ነው፡፡

በመንግስት በተለይ በኦሮሚያ ክልል በሚደርሱ የንጹሐን ጥቃቶች እጁ አለበት በሚል የሚወነጀለው ቡድን፣ በቅርቡ ከፌዴራል መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ ከሚገኘውና ሌላኛው በተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ሕወሓት ጋር በጋራ ለመስራት መስማማቱን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

አሁን ይፋ የተደረገው ምስጢራዊ የተባለው የፌስቡክ የአደገኛ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጥቁር መዝገብ ይፋ የተደረገው በራሱ በፌስቡክ ሳይሆን ‹ዘ ኢንተርሴፕት› በተባለው የኦንላይን ግብይት የሚደረግበት የኢቤይ አንደኛው መስራች በሆነው ፒየር ኦቢምያር በሚያስተዳድረው ድረ ገጽ ነው፡፡ ግዙፉ ፌስቡክ ይህን ምስጢራዊ ሰነድ ይፋ እንዲያደርገው በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ፈቃደኛ እንዳልነበር ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡

በዚሁ ይፋ በተደረገው ሰነድ ላይ በሽብርተኛነት ፈርጅ ላይ እስከ 50 በመቶ የሚሆኑ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከሙስሊም አገራት፣ ከደቡብ እስያ እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት የተቀመጡ ሲሆን፣ በአሜሪካ ውስጥ የሚገኙ የቀኝ ዘመም ታጣቂ ኃይሎችን ሰነዱ ቢያካትትም፣ ቀላል ገደብ ከሚጣልባቸው መካከል መድቧቸዋል፡፡

ምስጢራዊው የተባለው የአደገኛ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሰነድ ይፋ የተደረገበት ፌስቡክ፣ ባለፉት ቀናት በተለይ ከሚያራምደው ፖሊሲ እና ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ የተለያዩ ትችት አዘል አስተያየቶችን ሲያስተናግድ መሰንበቱ ይታወቃል፡፡

በኩባንያው ላይ ወቀሳ ካቀረቡት መካከል የሆኑት የቀድሞ ሠራተኛው የዳታ ሳይንቲስቷ ፍራንሴስ ሃውገን በአሜሪካ ሕግ አውጭ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ ሀገራት የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን መግታት እየቻለ አላስቆመም የሚል ውንጀላ ቀርቦበታል፡፡ የፌስቡክ የቀድሞ ሠራተኛ ይህን አካሄድ በመምረጡ በአገራቱ የበዛ ክፍፍል፣ በርካታ ውሸት እና ስጋት ማስከተሉን በመግለጽ፣ በኦንላይን ሚዲያው የሚሠራጩ አደገኛ ንግግሮች በሰዎች ላይ እስከ ሞት ማስከተላቸውንም አመልክተዋል፡፡

በተመሳሳይ ሶፊ ዣንግ የተባለች በፌስቡክ ኩባንያ ውስጥ የዳታ ሳይንቲስት ሆና ስትሰራ የቆየች ግለሰብ፣ መስርያ ቤቱ የሚሰራቸው ጥፋቶች ላይ ክስ ለማቅረብ እና ከዚህ ቀደም የነበሩበት ክሶች ላይ ለመመስከር የሚረዱ ሰነዶችን ለአሜሪካ ሕግ አስከባሪ ኤጀንሲ ማስተላለፏን ለሲኤንኤን ስትናገር ተደምጣለች፡፡

ፌስቡክ ከኢትዮጵያ ጋር በተገናኘ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ከኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውና ሐሰተኛና አሳሳች ይዘቶችን የሚያወጡ ናቸው ያላቸውን በርካታ ተያያዥ ገፆችና አካውንቶችን ማገዱን መስታወቁም አይዘነጋም፡፡

በዓለማችን በ111 ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጠው ግዙፉ የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ፌስቡክ፣ ይፋ ስለተደረገውና ምስጢራዊ ስለተባለው ሰነድ እና ተያያዥ ጉዳዮች በይፋ የሰጠው ማብራሪያ የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img