Thursday, November 21, 2024
spot_img

በምሥራቅ ወለጋ ባለፈው ቅዳሜ በደረሰ ጥቃት የበርካቶች ሕይወት መቀጠፉ ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥቅምት 3፣ 2014 ― በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መስከረም 29፣ 2014 በተነሳ ግጭት የበርካቶች ሕይወት ሲቀጠፍ፣ ሌሎች ደግሞ ግጭቱን ሸሽተው አካባቢውን ጥለው መውጣታቸውን አዲስ ስታንዳርድ ይዞት በዘገባው አመልክቷል፡፡

በእለቱ እኩለ ቀን ላይ ተጀምሯል ለተባለው ግጭት የዜና ድረ ገጹ አገኘኋቸው ያላቸው አንድ የአሮሞ ተወላጅ እና ሌላ የአማራ ተወላጅ የተለያየ መረጃ ሰጥተዋል፡፡

በዘገባው ሥማቸው የተቀየረ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ የዐይን እማኝ ጥቃቱን የፈጸሙት ወደ ኦሮሚያ ክልል የዘለቁ የአማራ ሚሊሻዎች ናቸው ያሉ ሲሆን፣ ለአንድ ሰአት የዘለቀ ጥቃት ፈጽመዋል ያሏቸው እነዚህ ሚሊሻዎች፣ ግጭቱን ቀድመው አቅደው ያስነሱት ነው ማለታቸው ተመላክቷል፡፡

እንደ ዐይን እማኙ ከሆነ በጥቃቱ 25 የኦሮሞ ተወላጆች ተገድለዋል፡፡ ጥቃት አድራሾቹ ከግድያ በተጨማሪ ዝርፊያ መፈጸማቸውን እንዲሁም መውሰድ ያልቻሉትን ደግሞ አቃጥለዋል፡፡  

ድረ ገጹ የጠቀሰው ሌላ የአማራ ተወላጅ የሆነ ዓይን እማኝ ደግሞ ጥቃቱ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ብቻ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ይልቁንም በሁለቱ ብሔሮች ማለትም በአማራ እና ኦሮሞ መካከል ነበር ብሏል፡፡

እንደዚህኛው የዓይን እማኝ ከሆነ ከጥቃቱ ጀርባ በስፍራው ይንቀሳቀሳል ያለውን በመንግስት ሸኔ የሚባለውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚለው ቡድን ሳይኖር እንዳልቀረ ነው ጥርጣሬውን ገልጧል፡፡ የዓይን እማኙ በግጭቱ ቢያንስ ሰባት የአማራ ተወላጆች ሲገደሉ፣ ሌሎች መቁሰላቸውን ገልጧል፡፡

ከነዚህ የዐይን እማኞች በተጨማሪ በዘገባው የተጠቀሱ የአገር ሽማግሌ እንዳሉት ደግሞ በአካባቢው የነበረው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አካባቢውን እንዳይለቁ ለአስተዳዳሪዎች ተናግረው የነበረ ቢሆንም፣ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ መስከረም 26፣ 2014 ል ኃይሉ ሥፍራውን መልቀቁን አስታውሰው፣ ግጭቱ የተከሰተውም የልዩ ኃሉ ከወጣ ከአራት ቀናት በኋላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጥቃቱ የበርካቶች ሕይወት እንደተቀጠፈ የገለጹት የአገር ሽማግሌ፣ ከሟቾቹ መካከል የሚበዙት የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው ብለዋል፡፡ የአገር ሽማግሌው ይህ እንደሚሆን ቀድመው ጠርጥረው የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ባለመደረጉ ጥፋቱን ማስከተሉንም አመለክተዋል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ የኪራሙ ወረዳ አስተዳዳሪ ደስታ ቲኪ በጉዳዩ ላይ መረጃ እንዲሰጡኝ ብጠይቅም ከመንግስት አቅጣጫ ካልተሰጠኝ መናገር አልችልም ብለውኛል ያለ ሲሆን፣ ሌሎች የክልሉ ባልስልጣናትም የሰጡት መረጃ የለም፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በመስከረም አጋማሽ ባወጣው መግለጫ በዚሁ አካባቢ የሚገኙ ሲቪል ሰዎች ለደኅንነታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆናቸው የሚያሳስብ መሆኑን ገለጾ ነበር።

 

 

ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ በኪራሙ ወረዳ ወረዳ፣ ቦቃ ቀበሌ መስከረም 7 እና 8፣ 2014 በደረሱ ሦስት ተያያዥ ጥቃቶች በአጠቃላይ 18 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን፤ እንዲሁም መስከረም 8፣ 2014 በውልማይ ቀበሌ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት 11 ሰዎች መገደላቸውን አሳውቆ ነበር፡፡  

 

 

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ደርሷል የተባለውን ጥቃት ተከትሎ በዛሬው እለት መግለጫ ያወጣው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በኪረሙ ወረዳ ሀሮ አዲስ አለም ቀበሌ በንፁሀን ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ማንነትን መሠረት ያደረገ መሆኑን በመግለጽ አውግዞታል፡፡



ፓርቲው በዞኑ ላለፉት ሶስት አመታት ሳያቋርጥ ዘልቋል ባለው ‹‹ዘር ተኮር ጥቃት›› በሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገለዋል፣ በመቶ ሺዎች ተፈናቅለዋል፣ በርካታ ሀብትና ንብረት ወድሟል ብሏል፡፡

አብን በአካባቢው መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ተቀዳሚ ተግባሩን እንዲወጣ፣ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፣ ለተጎጂዎችና የተጎጂ ቤተሰቦች ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግና በአስቸኳይ ፍትህ እንዲሰፍን ጠይቋል፡፡

 

 

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img